ኮርፖሬሽኑ ከመሬት ዝግጅት እስከ ጎተራ ድረስ አገልግሎት የሚሰጡ ዎኪንግ ትራክተሮችን አስመጣ
* ለተጠቃሚዎች የሚሰጠውን የአዲስ እርሻ መሬት ዝግጅት አገልግሎት ለማስፋትም ዶዘሮች እና ኤክስካቬተር አስገብቷል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 20 ቀን 2017 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፦ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከመሬት ዝግጅት እስከ ጎተራ ድረስ የሜካናይዜሽን አገልግሎት የሚሰጡ ዎኪንግ ትራክተሮችን አስመጣ፡፡20 የፈረስ ጉልበት ያላቸው እነዚህ ትራክተሮች የቻይና ስሪት ሲሆኑ፣ በኮርፖሬሽኑ ባለሞያዎች ተገጣጥመዋል፡
፡የኮርፖሬሽኑ የእርሻ መሣሪያዎች አቅርቦት እና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መንግሥቱ ክፍሌ እንደገለጹት፣ ትራክተሮቹ ለሰፋፊ የእርሻ መሬቶች እና ለአነስተኛ ማሳዎች ያገለግላሉ።
ለተጠቃሚዎች የሚቀርቡት እነዚህ ትራክተሮች የግብርና ሥራን ዘመናዊ እና ቀላል የሚያደርጉ፣ የአርሶ አደሩን ጉልበት የሚቆጥቡ እና ከበሬ ጫንቃ የሚያላቅቁ መሆናቸውን አቶ መንግሥቱ አስረድተዋል፡፡
ትራክተሮቹ ማረስ፣ መከስከስ፣ መዝራት፣ ማጨድ እንዲሁም ምርት፣ ዘር፣ አግሮኬሚካል እና ማዳበሪያ ማጓጓዝ፣ ውሃ ማጠጣት እና ሌሎችንም አገልግሎቶች መስጠት ይችላሉ።በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ ለተጠቃሚዎች የሚሰጠውን የአዲስ እርሻ መሬት ዝግጅት አገልግሎት ለማስፋት ዶዘሮች እና ኤክስካቬተር ከውጭ ማስገባቱን አቶ መንግሥቱ አስታውቀዋል፡፡
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!