የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን Ethiopian Agricultural Businesses Corporation

ለ2015/16 የሰብል ዘመን 573 ሺህ ኩንታል የሚጠጋ የአፈር ማዳበሪያ የጫነች የመጀመሪያዋ መርከብ ጅቡቲ ወደብ ደረሰች

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢግሥኮ) ለ2015/16 የሰብል ዘመን ከሞሮኮው የአፈር ማዳበሪያ አምራች ኦ ሲ ፒ ኩባንያ ከገዛው 7 ሚሊዮን 875 ሺህ 520 ኩንታል ማዳበሪያ (NPS family) ውስጥ የመጀመሪያው 572 ሺህ 950 ኩንታል NPS የአፈር ማዳበሪያ ጂቡቲ ወደብ ደረሰ።

ዛሬ ታህሳስ 18/2015 ዓ.ም. ከቀኑ 8:00 ላይ ወደብ የደረሰው ማዳበሪያ MV Great Comfort በተባለች የመጀመሪያዋ መርከብ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሰባት ቀን በኋላ (ታህሳስ 25/2015 ዓ.ም.) 600 ሺህ ኩንታል NPSB ማዳበሪያ የጫነች MV Sea Rider የተሰኘች ሁለተኛዋ መርከብ ጅቡቲ ወደብ እንደምትደርስ ይጠበቃል።

ኮርፖሬሽኑ ለያዝነው የሰብል ዘመን የገዛው 2 ሚሊዮን 188 ሺህ 940 ኩንታል NPS እና 5 ሚሊዮን 686 ሺህ 580 ኩንታል NPSB የአፈር ማዳበሪያ በቀጣዮቹ ወራት ከሞሮኮ ወደብ ወደ ጅቡቲ ይጓጓዛል። የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢግሥኮ) የግብርና ሚኒስቴር በየአመቱ አጥንቶ በሚያቀርበው ሀገራዊ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት መሰረት ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ ማዳበሪያ ከውጭ እየገዛ የሚያቀርብ መንግሥታዊ የልማት ድርጅት ነው።

ኮርፖሬሽኑ ከአውሮፓ ከሚያስመጣቸው 115 ትራክተሮች ውስጥ የመጀመሪያዎቹ 30 ትራክተሮች በቅርቡ አዲስ አበባ ይገባሉ

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢግሥኮ) በዚህ ዓመት ከአውሮፓ ከሚያስመጣቸው 115 ትራክተሮች ውስጥ የመጀመሪያዎቹን 30 ትራክተሮች ከአንድ ወር በኋላ ይረከባል፡፡

በኮርፖሬሽኑ የእርሻ መሣሪያዎችና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መንግሥቱ ክፍሌ እንደተናገሩት፣ ኮርፖሬሽኑ 11.7 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ግምት ያላቸውን የተለያዩ የእርሻ መሣሪያዎች፣ ተቀጽላዎች/Implements እና መለዋወጫዎች ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኤልሲ ከተከፈተላቸው የእርሻ መሣሪያዎች ውስጥ የቼክ ሪፐብሊክ ስሪት የሆኑት 115 ትራክተሮች እንደሚገኙበት የገለጹት አቶ መንግሥቱ፣ ከእነዚህ ውስጥ 30ዎቹ ትራክተሮች ከመጪው ጥር ወር አጋማሽ ጀምሮ አዲስ አበባ ይደርሳሉ ብለዋል፡፡

ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎች የሀገራችንን የግብርና አመራረት ዘዴ ለማዘመን ከፍተኛ ፋይዳ አላቸው ያሉት አቶ መንግሥቱ፣ ከዚህ አኳያ ትራክተሮቹ ለክልሎች፣ ለአርሶ አደሮች፣ በግብርና ሥራ ለተሰማሩ የግል ባለሃብቶች እና ለሌሎች ተጠቃሚዎች እንደሚቀርቡም አክለው አስታውቀዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የሚያስመጣቸው ‘ዜቶር’ በመባል የሚታወቁት ትራክተሮች ለአጠቃቀም ቀላል መሆናቸውን እንዲሁም የአጠቃቀምና አያያዝ ጉድለት ቢያጋጥም እንኳ በቶሎ እንደማይበላሹ የገለጸት ሥራ አስፈጻሚው፣ ብልሽት ካጋጠማቸውም በቀላሉ ሊጠገኑ እንደሚችሉ አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም ኮርፖሬሽኑ ከእርሻ መሣሪያዎች ሽያጭ በኋላ የጥገና፣ የቴክኒክ ሞያ ሥልጠና እና የመለዋወጫዎች አቅርቦት አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከ103 ሺህ ኩንታል በላይ የአርሶ አደሮችን እና የሌሎች ምርጥ ዘር አባዥዎችን ምርት በመሰብሰብ አስረከበ

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 14/2015 ዓ.ም (ኢግሥኮ) ፡- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢግሥኮ) የአርሶ አደሮች፣ የባለሃብቶች እና የመንግሥት  ተቋማት ምርጥ ዘር አባዥዎችን የደረሱ ሰብሎች በተመጣጣኝ ዋጋ በመሰብሰብ አስረከበ፡፡

በኮርፖሬሽኑ የእርሻ መሣሪያዎችና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መንግሥቱ ክፍሌ እንደተናገሩት፣ ኮርፖሬሽኑ እስከ ታህሳስ 12 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ 90 ሺህ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ አቅዶ ከ103 ሺህ ኩንታል በላይ የደረሰ ሰብል በመሰብሰብ ለደንበኞቹ አስረክቧል፡፡

በዋናነት ስንዴ፣ ገብስ እና ጎመን ዘር በኮምባይን ሀርቨስተር አጭደን፣ ወቅተን እና አጓጉዘን አስረክበናል ያሉት አቶ መንግሥቱ፣ ለኦሮሚያ ክልል ምርጥ ዘር ድርጅት፣ ለአየሁ እርሻ ልማት፣ ለአርሶ አደሮች እና ለኮርፖሬሽኑ ምርጥ ዘር ማባዣዎች አገልግሎቱ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

አክለውም የደረሱ ሰብሎች ሙሉ በሙሉ ተሰብስበው ጎተራ እስኪገቡ ድረስ የምርት መሰብሰቡን ሥራ እንደሚቀጥሉ አስታውቀው፣  በአጠቃላይ በዚህ ዓመት ለአርሶ አደሮች እና ሌሎች የሜካናይዜሽን አገልግሎት ፈላጊዎች 261 ሺህ ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

አገልግሎቱ በ13 አጭዶ መውቂያ መሣሪያዎች እንዲሁም ምርትን ወደ አውድማ እና ጎተራ በሚያጓጉዙ 10 ገልባጭ ተሽከርካሪዎች በመታገዝ እየተሰጠ መሆኑንም አመልክተዋል።

የምርት መሰብሰብ አገልግሎቱ በአርሲ፣ ባሌ፣ ሸዋ እና ጎጃም አካባቢዎች በስፋት እየተሰጠ መሆኑን የጠቆሙት አቶ መንግሥቱ፣ የምርት መሰብሰብ ሥራው ተረፈ ምርትን ለእንስሳት መኖ እንዲሆን በሚያስችል መልኩ በጥራት እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ ምርት ከመሰብሰብ ሥራ ጎን ለጎን በደንበኞች ጥያቄ መሰረት የእርሻ መሬት እያዘጋጀ ነው ያሉት አቶ መንግሥቱ፣ በዚህ ረገድ በዳውሮ ዞን ዴሳ ወረዳ የቅባት እህሎችን በማምረት ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ለተሰማራ ልማታዊ ባለሃብት እየተዘጋጀ የሚገኘው 1 ሺህ ሄክታር የእርሻ መሬት ይጠቀሳል ብለዋል፡፡

አያይዘውም እስከ ህዳር 12/2015 ዓ.ም ድረስ 130 ሄክታር የሚሆን መሬት ለእርሻ በሚመች መልኩ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡

በተመሳሳይ የእርሻ መሣሪያዎችና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ዘርፍ በኮርፖሬሽኑ የታማሻሎ ምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት 300 ሄክታር መሬት በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

የማሳ ዝግጅትን በተመለከተም የኢትዮ አግሪ ሴፍት አየሁ እርሻ ልማት 2 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ለማልማት ውል መገባቱን ያስታወቁት አቶ መንግሥቱ፣ የእርሻ መሣሪያዎችን የማጓጓዝ እና የማሰማራት ሥራ እየተከናወነ በመሆኑ በቅርቡ ሥራው እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡

የምርት መሰብሰብ ሥራን እና ሌሎች ውል የተገባባቸውን የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎቶች በብቃት እንዲፈጸሙ ለማስቻል በአመራር ደረጃ በመስክ ተገኝቶ ሠራተኞችን በማበረታታት የተሻለ የሥራ ተነሳሽነት መፍጠር እንደተቻለም ገልጸዋል።

ግብርናን ለማዘመን የሜካናይዜሽን አገልግሎትን በስፋት ተደራሽ ማድረግ ይገባል የሚሉት አቶ መንግሥቱ፣ ከዚህ አኳያም ኮርፖሬሽኑ በግንባታ ላይ የሚገኘውን የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና የሜካናይዜሽን አገልግሎት መስጫ ማዕከልን ጨምሮ ሌሎች ተጨማሪ አዳዲስ ማዕከላትን በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ለማቋቋም እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከሚሰጣቸው በርካታ አገልግሎቶች ውስጥ ከመሬት ዝግጅት እስከ ጎተራ የሚዘልቅ የተቀናጀ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ተጠቃሽ ሲሆን፣ ተቋሙ ይህን አገልግሎት በመስጠት ለምርትና ምርታማነት እድገት እና ግብርናን ለማዘመን በሚደረገው ሀገራዊ እንቅስቃሴ የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡

ኮርፖሬሽኑን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለማድረስ በበጀት ዓመቱ የተያዘውን እቅድ ማሳካት ይጠበቅብናል” የኢግሥኮ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢግሥኮ) በ2015 በጀት ዓመት ለመፈጸም ያቀዳቸው ሥራዎች እንዲሳኩ የጋራ ጥረት እንዲደረግ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሳሰቡ፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ክፍሌ ወልደማርያም ይህን ማሳሰቢያ የሰጡት፣ ከጥር 1 ቀን ጀምሮ ሥራ ላይ በሚውል የተከለሰ እቅድ ዙሪያ ከኮርፖሬሽኑ የሥራ ሓላፊዎችና ሠራተኞች ጋር በግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅርቦት ዘርፍ የስብሰባ አዳራሽ ዛሬ ታህሳስ 11 ቀን 2015 ዓ.ም. በተደረገ ውይይት ነው፡፡

በዚሁ ወቅት አቶ ክፍሌ፤ ኮርፖሬሽኑ ተወዳዳሪ፣ ውጤታማ እና ቀጣይነት ያለው ተቋም እንዲሆን ምንጊዜም ያልተቆጠበ ጥረት ማድረግ አለብን ብለዋል፡፡

አክለውም በ2015 በጀት ዓመት የታቀዱ ሥራዎች እንዲሳኩ የግብርና ማሳደጊያ ግብዓቶች እንዲሁም የእርሻ መሣሪያዎች እና መለዋወጫዎች ግዥ በወቅቱ በመፈጸም ለአርሶ አደሩ፣ ለባለሃብቱ እና ለልማት ድርጅቶች ማቅረብ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።

የኮርፖሬሽኑን ካፒታል በማሳደግ እና የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ተደራሽነት በማስፋት ተቋሙን ከፍተኛ ደረጃ ላይ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ለስኬቱም የኮርፖሬሽኑ የሥራ ሓላፊዎችና ሠራተኞች ‘በይቻላል እና  በጊዜ የለኝም’ የሥራ መንፈስ መረባረብ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

የኮርፖሬሽኑ የኦፕሬሽን ዐቢይ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፈለቀ ገዛኸኝ በበኩላቸው፣ ኮርፖሬሽኑ በሠራተኞቹ ብቃት እንደሚተማመን ገልጸው፣ የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድን ከመላው ሠራተኛ ጋር በመሆን እናሳካዋለን ብለዋል፡፡

አያይዘውም “እቅዱን ለማሳካት በጋራ ራዕይ አንድ ላይ መስራት እና ውጤት ማምጣት ይጠበቅብናል” በማለት ተናግረዋል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች በበኩላቸው የተቋሙ የሥራ አመራር ራዕይ ያለው፣ ሰርቶ የሚያሰራ፣ በእውቀት እና በቅንነት ሥራዎችን በአግባቡ የሚያከናውን መሆኑን ጠቁመው፤ የ2015 በጀት ዓመት ዕቅድን ለማሳካት እና የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በ2015 በጀት ዓመት ከ12 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን የግብርና ግብዓቶች፣ የእርሻ መሣሪያዎችና መለዋወጫዎች እንዲሁም የተቀናጀ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት እና የደረቅ ጭነት ትራንስፖርት በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚዎች በማቅረብ ከታክስ በፊት 995 ሚሊዮን ብር ለማትረፍ አቅዶ እየሰራ ይገኛል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ወቅታዊ ዓለም አቀፋዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች በኮርፖሬሽኑ የልማት እንቅስቃሴ ላይ ስለሚያሳድሩት ተጽዕኖ በዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ክፍሌ ወልደማርያም ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

የኮርፖሬሽኑ የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በሦስት ክልሎች በኮንትራት እርሻዎች ምርጥ ዘር እያባዛ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 8 ቀን 2015 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፡- በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በሦስት ክልሎች በኮንትራት እርሻዎች የተለያዩ ሰብሎች ምርጥ ዘር እያባዛ ይገኛል፡፡

የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ አድማሱ አናጋው እንዳስታወቁት፣ ጽ/ቤቱ በተያዘው የ2014/15 የመኸር ወቅት በኮንትራት አባዥ ሰፋፊ የባለሃብት እርሻዎች፣ በመንግሥት የግብርና ተቋማት እና በአርሶ አደር ማሳዎች ላይ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ እና ምስራቅ ሸዋ ዞኖች፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በጉራጌ፣ ስልጤ፣ ወላይታ፣ ሃድያ እና ሃላባ ዞኖች እንዲሁም በሲዳማ ክልል በድምሩ በስምንት ዞኖች በ2 ሺህ 34 ሄክታር መሬት ላይ የተለያዩ የሰብል ዝርያዎችን ምርጥ ዘር በማባዛት ላይ ይገኛል።

በዋናነት የስንዴ፣ ጤፍ፣ በቆሎ እና ቦለቄ ሰብሎችን ምርጥ ዘር እያባዛን ነው ያሉት አቶ አድማሱ፣ በዚህም 45 ሺህ 752 ኩንታል ዘር እንደሚገኝ ይገመታል ብለዋል፡፡

ዘር በከፍተኛ ጥንቃቄ ተመርቶ ለተጠቃሚዎች እንደሚቀርብ የገለጹት አቶ አድማሱ፣ ከዚህ አኳያ ከማሳ መረጣ ጀምሮ ምርት ተሰብስቦ መጋዘን እስኪገባ ድረስ የክትትልና የጥራት ቁጥጥር ሥራዎችን በመስክ በመገኘት እያከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።

የተለያዩ የሰብል ዘሮችን በማባዛት በመላ ሀገሪቱ እንደሚያሰራጩ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ በዚህ ወቅት እየተባዛ የሚገኘውን ምርጥ ዘር ጽ/ቤቱ በሀዋሳ ከተማ ባሉት ሁለት የዘር ማዘጋጃ ማሽኖች በማበጠርና በማዘጋጀት ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

አክለውም ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ በሻሸመኔ ከተማ ባለው የሽያጭ ማዕከል አማካኝነት የአፈር ማዳበሪያ፣ አግሮኬሚካሎች እና የእንስሳት መድሃኒቶችን ለአርሶአደሩ በቅርበት እያደረሰ መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል አርሶ አደሩ ከግብርና ምርምር የወጡ አዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን እንዲጠቀም ለማስቻል በተለያዩ አካባቢዎች የሰርቶ ማሳያ እና የአርሶ አደሮች በዓል በማዘጋጀት ዝርያዎቹን የማስተዋወቅ ሥራ በትኩረት እየተከናወነ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

### ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!

በኮርፖሬሽኑ የጎንዴ ኢተያ መስራች ዘር ማባዣ እርሻ ልማት እና በኮንትራት እርሻዎች ከ111 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 11/2015 ዓ.ም (ኢግሥኮ) በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በአሰላ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት አማካኝነት በጎንዴ ኢተያ መስራች ዘር ማባዣ እርሻ ልማት እንዲሁም በሰፋፊ የባለሃብትና የአርሶ አደር የኮንትራት እርሻዎች በዘር ከተሸፈነው 3 ሺህ 15 ሄክታር መሬት ከ111 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ ተገለጸ፡፡

የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ የሺጥላ እንደገለጹት፣ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የራሱ እርሻዎች በሆኑት የጎንዴ ኢተያ እንዲሁም በሰፋፊ የባለሃብት እርሻዎች እና በአርሶ አደር ማሳ የ11 ሰብል ዓይነቶች 38 ዝርያዎች እየተባዙ ይገኛሉ፡፡

በ2014/15 የመኸር ወቅት 1 ሺህ 561 ሄክታር መሬት በዘር ለመሸፈን ታቅዶ 3 ሺህ 15 ሄክታር በዘር ለመሸፈን ተችሏል ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ በዚህም ከ111 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል፡፡

የዘር ብዜት ሥራው በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ እና አርሲ ዞኖች እየተካሄደ እንደሚገኝ የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ በዋናነት በቢሾፍቱ፣ ወንጂ፣ ባቱ፣ በቆጂ እና ዴራ አካባቢዎች ባሉ ሰፋፊ እርሻዎችና ማሳዎች እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአበባ ደረጃ ያለ፣ ፍሬ መያዝ የጀመረ እና የደረሰ ሰብል አለ ያሉት አቶ ብርሃኑ፣ በወንጂ ሸዋ ስኳር ፋብሪካ የተዘራው የስንዴ ሰብል በመድረሱ እየተሰበሰበ ይገኛል ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል በአሰላ ከተማ በሚገኘው የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ዘር ማዘጋጃ ማሽን ለግብርና ምርምር ተቋማት፣ ለዘር አባዥዎች እና ለሌሎች ተጠቃሚዎች የዘር ብጠራ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

አክለውም የአፈር ማዳበሪያ፣ የአግሮኬሚካሎች እና የዘር ሽያጭ እያከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢግሥኮ) ስር የሚተዳደረው የአሰላ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በ1973 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን፤ በራሱ የመስራች ዘር ማባዣ እርሻ ጣቢያ እና በኮንትራት እርሻዎች እያባዛ ከሚገኘው ዘር በተጨማሪ ለአርሶ አደሩ፣ ለባለሃብቶች እና ለልማት ድርጅቶች የግብርና ማሳደጊያ ግብዓቶችን እያቀረበ ይገኛል፡፡

### ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!

ኮርፖሬሽኑ ከአርዳይታ እርሻ ልማት ከ85 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ይጠብቃል

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15/2015 ዓ.ም. (ኢግሥኮ):- በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ስር ከሚተዳደሩት እርሻዎች አንዱ በሆነው የአርዳይታ ምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት ከ85 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገለጸ፡፡

የአርዳይታ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ከበደ እንደገለጹት፣ በ2014/15 የመኸር ወቅት 3 ሺህ 70 ሄክታር መሬት በቅድመ መስራች፣መስራች እና የተመሰከረለት ዘር ደረጃዎች መሸፈን ተችሏል፡፡

ከዚህ ውስጥ 2 ሺህ 360 ሄክታር በስንዴ፣ 612 ሄክታር በጎመን ዘር፣ 67 ሄክታር በገብስ እና 31 ሄክታር በባቄላ ዝርያዎች መሸፈኑን አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ሰብል በእሸት እና አበባ ደረጃ ይገኛል ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ የሰብሎቹ ሁኔታ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ የተለየ ተፈጥሮአዊ ችግር ካላጋጠመ በስተቀር ያቀዱትን ከ85 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚያሳኩ አስታውቀዋል፡፡

የአርዳይታ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በቅድመ መስራች፣ መስራች እና የተመሰከረለት የዘር ደረጃ 33 የስንዴ፣ ዘጠኝ የገብስ፣ አንድ የባቄላ እና አንድ የጎመን ዘር ዝርያዎችን እያባዛ ይገኛል፡፡

በሌላ በኩል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር ለአካባቢው ነዋሪዎች የተለያዩ ድጋፎችን እና ትብብሮችን እያደረገ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ፍቃዱ፣ ለአካባቢው አርሶ አደሮች ዘር ከመሸጫ ዋጋ አምስት በመቶ ቅናሽ በማድረግ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በየዓመቱ በአረም እና ምርት መሰብሰቢያ ወቅት ከ800 እስከ 1000 ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ እድል እንደሚፈጠርም አስረድተዋል፡፡

ተረፈ ምርትን ወይም የሰብል ገለባን በማኅበር ለተደራጁ የአጎራባች ቀበሌ ሥራ አጥ ወጣቶች በመስጠት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ያለውን ድጋፍም አመልክተዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር በቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ክሊኒክ ለአካባቢው ነዋሪዎች በቅናሽ ዋጋ የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና እርዳታ፣ ነጻ የማዋለድ እና የአምቡላንስ አገልግሎት ድጋፍ እየተሰጠ መሆኑንም አክለው አስታውቀዋል፡፡

የአርዳይታ ምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት ኮርፖሬሽኑ በስሩ ካሉት እርሻዎች መካከል በስፋት ትልቁ ሲሆን፣ መገኛውም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ገደብ አሳሳ ወረዳ ነው፡፡

### ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!

ኮርፖሬሽኑ የምርጥ ዘር አቅርቦትን ለማሳደግ ከባለሃብቶች ጋር እየሰራ ነው

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 17 ቀን 2015 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፡- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለተጠቃሚዎች የሚያቀርበውን ምርጥ ዘር በጥራትና በመጠን ለማሳደግ በኮንትራት ሰፋፊ እርሻዎች ከባለሃብቶች ጋር እየሰራ ነው።

የይስሃቅ ሳምሶን እርሻ ልማት እና የዱቄት ፋብሪካ ባለቤት አቶ ይስሃቅ ሳምሶን ከኮርፖሬሽኑ ጋር ምርጥ ዘር ማባዛት ከጀመሩ ሶስት ዓመት እንደሆናቸው ገልጸው፣ በዚህ ዓመት ከኮርፖሬሽኑ ኮፈሌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር ውል በመግባት በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ባሌ ዞን ጊኒር እና ጃራ ወረዳዎች 210 ሄክታር መሬት በሰብል በመሸፈን ዘር እያባዙ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

” ኮርፖሬሽኑ ባለሞያዎችን እየላከ ድጋፍና ክትትል ስለሚደርግልን ምርታማነታችን ከፍ እንዲል አድርጓል” ያሉት አቶ ይስሃቅ፣ በትብብር መስራታቸው ምርታማነታቸውን በመጨመሩ ወደፊትም ከኮርፖሬሽኑ ጋር መስራት ምርጫቸው እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

አክለውም ሰፊውን አርሶ አደር ዘር በማባዛት ለመጥቀም እና በምላሹም ለዱቄት ፋብሪካቸው ግብዓት የሚሆን ምርት ከአርሶ አደሩ ለመሰብሰብ የዘር ብዜት ሥራ ውስጥ መግባታቸውን አብራርተዋል፡፡

ሌላኛው የቡላላ ዲኒቂቲ እርሻ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መኮንን ጸጋየ የተሻለ ዘር በማምረት መንግሥትን እና ሕዝብን ለመደገፍ በሚል ሃሳብ ዘር በማባዛት ሥራ ላይ መሰማራታቸውን ጠቁመው፣ ከ1995 ዓ.ም ጀምሮ አሁን በኮርፖሬሽኑ ስር ከሚገኘው የኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ድርጅት ጋር ውል በመግባት ዘር እያባዙ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡

እንደ ሥራ አስፈጻሚው ገለጻ፣ በ2014/15 የመኸር ወቅት ከኮፈሌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር ውል በመግባት በምስራቅ ባሌ ዞን ጊኒር እና ጎሎልቻ ወረዳዎች ከ1 ሺህ 200 ሄክታር በላይ መሬት ላይ የተለያዩ የሰብል ዝርያችዎችን በማባዛት ላይ ናቸው ።

የኮርፖሬሽኑ ባለሞያዎች ከእርሻ ሥራ ጀምሮ ምርት እስኪሰበሰብ ድረስ ከእኛ ጋር ናቸው ያሉት አቶ መኮንን፣ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በመስራታቸው ትርፋማ መሆናቸውን መስክረዋል፡፡ በተጨማሪም ያባዙትን ምርት ኮርፖሬሽኑ በራሱ ትራንስፖርት እና ከረጢት እንደሚረከባቸው ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዓመት ከሌላው ጊዜ የተሻለ የዝናብ ሥርጭት መኖሩን የተናገሩት አቶ መኮንን፣ ሰብሉ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ጥራት ያለው ዘር አባዝተው ለኮርፖሬሽኑ ለማስረከብ እየሰሩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

በሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ኤልፎራ አግሮ ኢንዱስትሪ የኤልፎራ ነትሌ እርሻ ሥራ አስኪያጅ አቶ በኃይሉ ምትኩ በበኩላቸው፣ እንደ ሀገር ያለውን የበቆሎ ዘር እጥረት ለመቅረፍ እና በግብርናው ዘርፍ የራሳቸውን አስተዋጽዖ በማበርከት ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ከኮርፖሬሽኑ የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር 120 ሄክታር መሬት ላይ በቆሎ እያለሙ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

ከኮርፖሬሽኑ ጋር የቆየ ግንኙኘት እንዳላቸው የተናገሩት አቶ በኃይሉ፣ ከዚህ አኳያም ኮርፖሬሽኑን እንደራሳቸው ድርጅት እንደሚቆጥሩት ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ ከኮርፖሬሽኑ ጋር የተለያዩ ሰብሎችን ዘር እያባዛን እንገኛለን ብለዋል።

ምርጥ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያ እና አግሮኬሚካሎችን ኮርፖሬሽኑ እንደሚያቀርብላቸው ገልጸው፣ የሜካናይዜሽን አገልግሎት በመስጠትም የኤልፎራ ነትሌ መሬትን ለእርሻ ዝግጁ ማድረጉን ጠቁመዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ግብርናን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እያደረገ ያለው ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራ ለወገንም ሆነ ለሀገር በጣም ጠቃሚ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ ወደፊትም ከኮርፖሬሽኑ ጋር መስራታችንን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

የኢቲኤም ጠቅላላ የግብርና ሥራ ባለቤት አቶ መስፍን ነጋሽ በበኩላቸው፣ የተለያዩ ሰብሎችን ምርጥ ዘር በብዛትና በጥራት በማባዛት ለአካባቢው አርሶ አደሮች ዘር ለማቅረብ የዘር ብዜት ሥራን በ1994 ዓ.ም መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከኮርፖሬሽኑ የአሰላ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ጋር በመተባበር በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን አድአ ወረዳ በ76 ሄክታር መሬት ላይ ጤፍ እና ሽንብራ እያባዙ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

“ከኮርፖሬሽኑ ጋር እንደ ቤተሰብ ነው ተባብረን የምንሰራው” ያሉት አቶ መስፍን፣ የአሰላ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከእርሻ ማሳ ዝግጅት ጀምሮ ምርት እስኪሰበሰብ ድረስ ክትትል እንደሚያደርግላቸው እና ለሚያጋጥማቸው ችግርም መፍትሔ እንደሚሰጣቸው አስታውቀዋል፡፡

ከዚህ አኳያ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በመስራታቸው ውጤታማ መሆናቸውን የሚናገሩት አቶ መስፍን፣ በ2007 ዓ.ም ከቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እጅ በምርጥ ዘር ብዜት ሥራ የመንግሥት አጋዥ በመባል ሽልማት መቀበላቸውን አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከራሱ እርሻዎች በተጨማሪ በኮንትራት አማካይነት በሰፋፊ የመንግሥትና የባለሃብት እርሻዎች እንዲሁም በአርሶ አደሮች ማሳዎች ላይ ዘር በማባዛት እና በማዘጋጀት ለተጠቃሚዎች እያቀረበ የሚገኝ የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው፡፡

### ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!

ኮርፖሬሽኑ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ62 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን ለተጠቃሚዎች አቅርቧል

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በ2014 በጀት ዓመት ከ62 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን ለተጠቃሚዎች አቅርቧል፡፡

በኮርፖሬሽኑ የግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅርቦት ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ገብሬ እንደገለጹት፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ኮርፖሬሽኑ ምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩ የአፈር ማዳበሪያ፣ የሰብል ተባይ ማጥፊያ አግሮኬሚካሎች እና ኬሚካል መርጫ መሣሪያዎችን ከዓለም አቀፍ አቅራቢዎች በመግዛት ለተጠቃሚዎች ማቅረብ ችሏል፡፡

በዚህ መሰረት ለ2014/15 የሰብል ዘመን የሚውሉ 61 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ዋጋ ያላቸው 12 ሚሊዮን 876 ሺህ 620 ኩንታል ዩሪያ፣ ኤን ፒ ኤስ እና ኤን ፒ ኤስ ቢ የአፈር ማዳበሪያዎች ለአርሶ አደሮች፣ ለከፊል አርብቶ አደሮች እና በግብርናው ዘርፍ ለተሰማሩ ባለሃብቶች መቅረቡን ነው ሥራ አስፈጻሚው ያስታወቁት፡፡

በተጨማሪም ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ፈሳሽ እና ዱቄት አግሮኬሚካሎች እና 3 ሺህ 870 የኬሚካል መርጫ መሣሪያዎች ለተጠቃሚዎች ተደራሽ መደረጋቸውን አቶ ሰለሞን ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም 58 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ዋጋ ያላቸው የእንስሳት መድሃኒቶች ሽያጭ መከናወኑንም ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የአፈር ማዳበሪያ እና አግሮኬሚካሎች በኮርፖሬሽኑ መጋዘኖች እንደሚገኙ የጠቆሙት አቶ ሰለሞን፣ ተጠቃሚዎች ግብዓቶችን በመግዛት ምርትና ምርታማነታቸውን ማሳደግ እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡

በቀጣይም ተጨማሪ ደረጃቸውን የጠበቁ የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብዓቶች በብዛት እንደሚቀርቡ አመልክተው፣ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የአግሮኬሚካሎች ግዥ በሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

በ2014 በጀት ዓመት በኮርፖሬሽኑ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ለተጠቃሚዎች ከቀረቡ የግብርና ምርት ማሳደጊያዎች ግብዓት ሽያጭ፣ ከአገልግሎት ክፍያ እና ከልዩ ልዩ ገቢዎች ከ3 ቢሊዮን 416 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መገኘቱንም ሥራ አስፈጻሚው አክለው አስታውቀዋል፡፡                                                              ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!

አቶ ሰለሞን ገብሬ
የግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅርቦት ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ