የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን Ethiopian Agricultural Businesses Corporation

ኮርፖሬሽኑ ከውጭ ያስመጣቸውን ትራክተሮች ለፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ በሽያጭ አስረከበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29/2016 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፡- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከአውሮፓ ካስመጣቸው ‘ዜቶር’ ትራክተሮች ውስጥ ስምንት ትራክተሮችን ከእነተቀጽላቸው ‘ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ’ በመባል ለሚታወቅ ድርጅት በሽያጭ አስረከበ፡፡ ድርጅቱ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ስምንት ትራክተሮችን፣ ስምንት ማረሻዎችን፣ ሦስት መከስከሻዎችን እና ሦስት መስመር ማውጫዎችን ከኮርፖሬሽኑ ገዝቷል።  ዛሬ ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም በኮርፖሬሽኑ ዋና መስሪያ ቤት በተካሄደ የርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም ለፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍስሀ እሸቱ (ዶ/ር) የትራክተሮቹን ቁልፍ አስረክበዋል፡፡

አቶ ክፍሌ በሥነ ሥርዓቱ ወቅት ይፋ እንዳደረጉት፣ በቀጣይ ለአማራ ክልል የ75 ዜቶር ትራክተሮች ርክክብ እንደሚደረግ ይጠበቃል። ኮርፖሬሽኑ የሀገሪቷን ግብርና ለማዘመን ጥራት ያላቸውን አስተማማኝ የእርሻ መሣሪያዎች ከአውሮፓና ከቻይና እያስመጣ ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ይገኛል ያሉት አቶ ክፍሌ፣ ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ የተረከባቸው የቼክ ሪፐብሊክ ስሪት የሆኑት ዜቶር ትራክተሮች የግብርና ምርታማነትን እንደሚያሳድጉ አስታውቀዋል፡፡ አክለውም ኮርፖሬሽኑ ለገበያ ለሚያቀርባቸው ዜቶር ትራክተሮች እና ሌሎች የእርሻ መሣሪያዎች ከሽያጭ በኋላ በዋናው መ/ቤት እና በክልሎች ባሉት 25 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የጥገና አገልግሎት እንደሚሰጥ እና መለዋወጫዎች እንደሚያቀርብ  አረጋግጠዋል። የፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍስሀ እሸቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው ድርጅታቸው ከኮርፖሬሽኑ ጋር ዘርፈ ብዙ የሥራ ግንኙነት እንዳለው ጠቁመው፣ በምርጥ ዘር ብዜት ከኮርፖሬሽኑ ጋር በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ተደራሽ እና አስተማማኝ የሆነ አገልግሎት ስለሚሰጥ ትራክተሮቹን ከኮርፖሬሽኑ ለመግዛት እንደወሰኑ የገለጹት ፍስሀ እሸቱ (ዶ/ር)፣ በቀጣይም  ተጨማሪ ትራክተሮችን እንደሚገዙ ጠቁመዋል፡፡ በተመሳሳይ በመሬት ዝግጅት፣ በግብርና ግብዓት አቅርቦት እና በሌሎችም የዘርፉ አገልግሎቶች ከኮርፖሬሽኑ ጋር በትብብር መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ አያይዘው ገልጸዋል፡፡ ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ በግብርና፣ በምግብ ማቀናበር፣ በሪል ስቴት፣ በችርቻሮ ንግድ እና በሌሎች መስኮች የተሰማራ ድርጅት ነው፡፡

ኮርፖሬሽኑ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኮንትራት እርሻ እያባዛ የሚገኘውን የድቃይ በቆሎ የተመሰከረለት የዘር ማሳ አስጎበኘ

ኮርፖሬሽኑ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኮንትራት እርሻ እያባዛ የሚገኘውን የድቃይ በቆሎ የተመሰከረለት የዘር ማሳ አስጎበኘ * የክልሉ መንግሥት ኮርፖሬሽኑ ላቀረበው ተጨማሪ የዘር ማባዣ መሬት ጥያቄ ምላሽ እንደሚሰጥ አስታውቋል ============================ አሶሳ፣ ጥቅምት 27/2016 ዓ.ም (ኢግሥኮ):- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኮንትራት እርሻ  ከባለሀብት ጋር እያባዛ የሚገኘውን የድቃይ በቆሎ የተመሰከረለት የዘር ማሳ ለክልል፣ ዞን፣ ወረዳ እና ቀበሌ አመራሮች ጥቅምት 27 ቀን 2016 ዓ.ም አስጎበኘ። ከክልሉ ዋና ከተማ አሶሳ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የአሶሳ ዞን አብረሃሞ ወረዳ በተዘጋጀው የመስክ ጉብኝት እና በአሶሳ ከተማ ባምቡ ፓራዳይዝ ሆቴል በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ  አጥናፉ  አጎናፍር ፣ የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበከር ሀላፋ፣ የግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አጥናፉ ባቡር እንዲሁም ሌሎች የቢሮ፣ የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ  አመራሮች እና የግብርና ባለሞያዎች ተገኝተዋል። በእንግዶች የተጎበኘው BH 546 በመባል የሚጠራው የድቃይ በቆሎ የተመሰከረለት ዘር ማባዣ ማሳ ሲሆን፣ ኮርፖሬሽኑ አቶ ሞላ ተመስገን ከተባሉ ባለሀብት ጋር በ146 ሄክታር መሬት ላይ በጋራ እያለመ የሚገኘው የኮንትራት እርሻ ነው። ይህንን እርሻ ጨምሮ ኮርፖሬሽኑ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በእሶሳ ዞን አምስት አካባቢዎች በ328 ሄክታር መሬት ላይ ድቃይ በቆሎ እና ድቃይ ያልሆነ በቆሎ የተመሰከረለት ዘር እያባዛ እንደሚገኝ እና 12 ሺህ ኩንታል ዘር እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት ለኮርፖሬሽኑ የዘር ማባዣ 1500 ሄክታር መሬት መፍቀዱን ያስታወሱት አቶ ክፍሌ፣ በሀገሪቷ እና በክልሉ ካለው የዘር ፍላጎት አንጻር ተጨማሪ 3500 ሄክታር የዘር ማባዣ መሬት አሶሳ ዞን ላይ እንዲሰጣቸው የክልሉን መንግሥት ጠይቀዋል። “ተጨማሪ መሬት ካገኘን በክልሉ የግብርና ግብዓት አቅርቦት እና የሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል እናቋቁማለን” ያሉት አቶ ክፍሌ፣ የማዕከሉ መቋቋም በክልሉ እና በአቅራቢያው የሚገኙ አርሶ አደሮች እና በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች የግብርና ግብዓቶችን፣ የእርሻ መሣሪያዎችን እና መለዋወጫዎችን እንዲሁም የሜካናይዜሽን፣ የጥገና፣ የምክር እና የቴክኒክ ሞያ አገልግሎቶችን በቅርበት ለማግኘት እንደሚያስችላቸው አስረድተዋል። በኮርፖሬሽኑ ለቀረበው ተጨማሪ የዘር ማባዣ መሬት ጥያቄ የክልሉ መንግሥት ምላሽ እንደሚሰጥ የግብርና ቢሮ ኃላፊው አቶ ባበከር ሀላፋ አስታውቀዋል። በጉብኝቱ ላይ የተገኙት በአሶሳ ዞን የአብረሃሞ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አቡዱላጢፍ አፉዲ፣ ኮርፖሬሽኑ በክልሉ ውስጥ የሚታየውን የዘር ችግር ለመቅረፍ የሚያደረገውን ጥረት አድንቀው፣ ልማቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። አክለውም ኮርፖሬሽኑ ትራክተሮች እና የግብርና ግብዓቶችን በስፋት ካቀረበላቸው በወረዳ ደረጃ የተሻለ ውጤት እንደሚያመጡ ገልጸዋል።  የመስክ ጉብኝቱ እና የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፣ ኮርፖሬሽኑ በአዘጋጀው መርሀ ግብር ልምድ እንዳገኙ እና ስለ ኮርፖሬሽኑም የሥራ እንቅስቃሴ ግንዛቤ እንደጨበጡ ተናግረዋል። ኮርፖሬሽኑ በክልሉ ውስጥ የልማት እንቅስቃሴ ማካሄዱ የክልሉን ግብርና በማዘመን የአርሶ አደሩን የግብዓት ችግር ለመቅረፍ እንደሚረዳም አመልክተዋል። በመስክ ጉብኝቱ ወቅት ቴክኒካዊ ማብራሪያ የሰጡት  አቶ በሊና ብርሃኑ በኮርፖሬሽኑ የነቀምት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ እንዳስረዱት፣ BH 546 የድቃይ በቆሎ የተመሰከረለት ዘር ከነባር ዝርያዎች በተሻለ ከፍተኛ ምርት ከመስጠቱ ባሻገር በሽታን የመቋቋም አቅሙ ከፍተኛ ነው። የኮርፖሬሽኑን አጠቃላይ ገጽታ በተመለከተም የኮርፖሬት ኦፕሬሽን ዐቢይ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፈለቀ ገዛኸኝ ለተሳታፊዎች ገለጻ አድርገዋል። በወቅቱ በተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በሀገር ደረጃ በምርጥ ዘር አቅርቦት ፋና ወጊ የሆነው የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ በተለያዩ ክልሎች የራሱን አምስት የምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት ጣቢያዎችን በማቋቋም እንዲሁም በሰፋፊ የመንግሥትና የግል እርሻዎች እና በክላስተር በተደራጁ አርሶ አደሮች ማሳ በኮንትራት በመስራት በአጠቃላይ በ15 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የ22 ሰብሎችን 78 ዝርያዎች እያባዛ በዓመት ከ350 ሺህ ኩንታል በላይ ዘር ለተጠቃሚዎች እያቀረበ ይገኛል፡፡ ይህም በሀገር ደረጃ ካለው የምርጥ ዘር ፍላጎት ውስጥ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነውን ድርሻ እንዲያሟላ አስችሎታል፡፡
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!

ኮርፖሬሽኑ ከአውሮፓ ከሚያስመጣቸው 75 ትራክተሮች ውስጥ 59ኙን ተረከበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22/2016 ዓ.ም. (ኢግሥኮ)፡- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከአውሮፓ ከሚያስመጣቸው 75 ትራክተሮች ውስጥ 59ኙን ተረከበ።

በኮርፖሬሽኑ የእርሻ መሣሪያዎች አቅርቦት፣ ማርኬቲንግና ሽያጭ መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጎሳዬ ቶሎሳ እንዳስታወቁት፣ ኮርፖሬሽኑ የሀገሪቷን ግብርና ለማዘመን የሚያስችሉ የእርሻ መሣሪያዎችን ከእነተቀጽላቸው ከአውሮፓ እና ከቻይና እያስመጣ ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከ110 እስከ136 የፈረስ ጉልበት ያላቸውን  ‘ዜቶር’ በመባል የሚታወቁ ትራክተሮችን ከቼክ ሪፐብሊክ እያስመጣ መሆኑን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ ከታዘዙ 75 ትራክተሮች ውስጥ እስከአሁን 59ኙን መረከባቸውን አስታውቀዋል፡፡ ቀሪዎቹ 16 ትራክተሮችም በቅርቡ  ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡

ዜቶር ትራክተር ላይ የቴክኒክ ብልሽት ቢያጋጥም መለስተኛ የእጅ መሣሪያዎችን በመጠቀም በቀላሉ መጠገንና ማስተካከል እንደሚቻልም አስረድተዋል። ኮርፖሬሽኑ ትራክተሮችን ከማቅረብ ባሻገር ከሽያጭ በኋላ ለደንበኞች የቴክኒክና ሞያ ሥልጠና፣ የጥገና እና የምክር አገልግሎቶች አዲስ አበባ በሚገኘው የቴክኒክና ሞያ ማሠልጠኛ ማዕከል እና በቅርንጫፎቹ እየሰጠ ይገኛል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የአርሶ አደሮች እና የባለሀብቶች ሰብል እየሰበሰበ ነው

ለመተሃራ ስኳር ፋብሪካ 700 ሄክታር የሸንኮራ አገዳ ማሳ እያዘጋጀ ይገኛል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23/2016 ዓ.ም. (ኢግሥኮ)፡- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የአርሶ አደሮችን፣ በግብርና ሥራ የተሰማሩ ባለሀብቶችን እና የተለያዩ ድርጅቶችን የደረሰ ሰብል በተመጣጣኝ ዋጋ እየሰበሰበ ነው፡፡በኮርፖሬሽኑ የእርሻ መሣሪያዎች እና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መንግሥቱ ክፍሌ እንደገለጹት፣ ኮርፖሬሽኑ ከጥቅምት 2016 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ በሞጆ እና ሄረሮ ዙሪያ ለሚገኙ አርሶ አደሮች እና ባለሀብቶች የሰብል መሰብሰብ ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡የሀገሪቱ የግብርና ምርት ሙሉ በሙሉ እስኪሰበሰብ ድረስ ኮርፖሬሽኑ አገልግሎቱን እንደሚቀጥል የተናገሩት አቶ መንግሥቱ፣ ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ በጎጃም የአየሁ እርሻ ልማት የደረሰ ሰብል እንደሚሰበሰብ ተናግረዋል፡፡እንደ ሥራ አስፈጻሚው ማብራሪያ፣ ኮርፖሬሽኑ በ10 አጭዶ መውቂያ መሣሪያዎች የሰብል መሰብሰብ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ አገልግሎቱን ለማጠናከር ተጨማሪ 10 አጭዶ መውቂያዎችን ከውጭ አስመጥቶአል።

አቶ መንግሥቱ ክፍሌ

በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ የመተሃራ ስኳር ፋብሪካን ነባር የሸንኮራ አገዳ በማስወገድ ለአዲስ የሸንኮራ አገዳ ተከላ 700 ሄክታር መሬት እያዘጋጀ መሆኑን አቶ መንግሥቱ አክለው አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በክልሎች ካሉት 25 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ውስጥ የሞጆ፣ ሄረሮ እና ቡሬ ጣቢያዎች በዋናነት የተቀናጀ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ለማስፋፋት እና ለማጠናከር የተቋቋሙ ናቸው፡፡

ኮርፖሬሽኑ በትራክተር የሚጎተቱ ጣልያን ሰራሽ የኬሚካል መርጫ ማሽኖችን አስመጣ

ከቻይናው ዙምላይን የገዛቸው ኮምባይን ሀርቨስተሮችም ጂቡቲ ወደብ ደርሰዋል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 19/2016 ዓ.ም (ኢግሥኮ):-የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢግሥኮ) በትራክተር የሚጎተቱ 15 ጣልያን ሰራሽ የኬሚካል መርጫ ማሽኖችን በ425 ሺህ 280 የአሜሪካን ዶላር (23 ሚሊዮን 605 ሺህ 251.456 ብር) አስመጣ።
በእርሻ መሣሪያዎች እና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ዘርፍ የእርሻ መሣሪያዎች አቅርቦት፣ ማርኬቲንግና ሽያጭ መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጎሳዬ ቶሎሳ እንዳስታወቁት፣ እያንዳንዱ ማሽን 3 ሺህ ሊትር አግሮኬሚካሎችን የመያዝ አቅም አለው።አክለውም ማሽኖቹ 24 ሜትር ስፋት እና ቁመታቸውም እስከ 2 ሜትር ከፍ እንደሚል ገልጸዋል።በሌላ ዜና ኮርፖሬሽኑ ከቻይናው ዙምላይን የእርሻ መሣርያ አምራች ኩባንያ ጋር ሰኔ 25/2015 ዓ.ም በገባው የንግድ ስምምነት መሰረት የገዛቸው 10 ኮምባይን ሀርቨስተሮች ጂቡቲ ወደብ መድረሳቸውን አቶ ጎሳ ተናግረዋል።ኮምባይን ሀርቨስተሮቹ በ648 ሺህ 600 የአሜሪካን ዶላር (36 ሚሊዮን 672 ሺህ 72 ብር) መገዛታቸውን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ፣ በቅርቡ ወደ ሀገር ውስጥ ተጓጉዘው ለ2015/16 የምርት ዘመን የአጨዳ ሥራ እንደሚደርሱ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በአቢሲኒያ የጥራት ሽልማት ድርጅት የተዘጋጀውን የመጀመሪያ የኢንደስትሪ ሽልማት አገኘ።

በኢንተርሌግዠሪ ሆቴል መጋቢት 24/2015 ዓ.ም. በተዘጋጀ የኢንደስትሪ ሽልማት መርሐ ግብር ላይ ኮርፖሬሽኑ የወርቅ ዋንጫ፣ የወርቅ ሜዳሊያ እና ከፍተኛ የክብር ዲፕሎማ አግኝቷል። ሽልማቱን ከዕለቱ የክብር እንግዳ የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) እጅ የተቀበሉት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም ናቸው።

በተመሳሳይ  የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም በግላቸው የሥራ አመራር ከፍተኛ የክብር ኮርደን/GOLD Honor CORD ሽልማት እና በኢንደስትሪ ሥራ አመራር የላቀ አፈጻጸም የክብር ዲፕሎማ (Diploma of the Legion of Honour) ከቀድሞ ፕሬዝዳንት እጅ ተቀብለዋል። እንዲሁም የኮርፖሬሽኑ የኦፕሬሽን ዐቢይ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፈለቀ ገዛኸኝ ከቀድሞ ፕሬዝዳንት እጅ  የወርቅ ኒሻንና የትጉህ አመራር የክብር ዲፕሎማ ተሸልመዋል። በተጨማሪም ሦስት አመራሮችና ዘጠኝ ሠራተኞች የወርቅ ሜዳሊያና የትጉህ ሠራተኝነት የክብር ዲፕሎማ ከአቢሲኒያ የጥራት ሽልማት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አሰፋ ከሲቶ እጅ ተቀብለዋል።

በሽልማት መርሐ ግብሩ ላይ የዕለቱን የክብር እንግዳ የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ የኢንደስትሪ ተቋማት አመራሮች፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ ተሽላሚዎችና ቤተሰቦቻቸው ተገኝተዋል። በኮርፖሬሽኑ በኩል በሽልማት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ወልደአብ ደምሴ፣ በሠራተኛ የተመረጡ የቦርድ አባላት፣ የመሰረታዊ የሠራተኛ ማኅበር ሓላፊዎች፣ የማኔጅመንት አባላት እና ሠራተኞች ተገኝተዋል።

“ዓለምንና ሕዝቦቿን የሚታደግ የላቀ ሥራ ለሰሩ ትጉሃን እንሸልማለን!” የሚል መሪ ቃልን አንግቦ በተለያዩ የሞያ መስኮች መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦችን በየዓመቱ በመሸለም የሚታወቀው “አቢሲኒያ ዓለም አቀፍ ሽልማት ድርጅት” ከ2010 እስከ 2014 ዓ.ም. ድረስ ባደረገው ጥናት ለመጀመሪያ ጊዜ ለኢንደስትሪ ሽልማት ካጫቸው ከ57 ሺህ በላይ አምራች እና አገልግሎት ሰጪ የመንግሥት፣ የግል እና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ውስጥ 50 ተሸላሚዎችን የመረጠ ሲሆን፣  የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢግሥኮ) አንዱ በመሆን ተሸልሟል።

በአቢሲኒያ የጥራት ሽልማት ድርጅት የተሸለሙ የኢግሥኮ ትጉሃን የሥራ አመራሮችና ሠራተኞች ስም ዝርዝር

1.
 አቶ ክፍሌ ወልደማርያም
2. አቶ ፈለቀ ገዛኸኝ
3. አቶ ዘነበ ወልደሥላሴ
4. አቶ ሰለሞን ገብሬ
5. ወይዘሮ መንበረ ኃይለማርያም
6. ወይዘሮ አመለወርቅ ዓለምአየሁ – ከግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅርቦት ዘርፍ
7. ወይዘሮ ነፃነት ረቡማ – ከግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅርቦት ዘርፍ
8. አቶ ተስፋሁን አበበ አንጀሎ – ከእርሻ መሣሪያዎችና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ዘርፍ
9. አቶ ሲራክ ደገፋ – ከእርሻ መሣሪያዎችና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ዘርፍ
10. አቶ ሲዳ ለታ – ከኢትዮጵያ ምርጥ ዘር እና ደን ውጤቶች ዘርፍ
11. አቶ ሻምበል ገላን – ከኢትዮጵያ ምርጥ ዘር እና ደን ውጤቶች ዘርፍ
12. አቶ ግርማ ፋሪስ – ከተሽከርካሪዎች አስተዳደርና ጥገና ዘርፍ
13. አቶ ተከስተ ተክሌ – ከተሽከርካሪዎች አስተዳደርና ጥገና ዘርፍ
14. አቶ ዳንኤል ስንሻው – ከዋናው መ/ቤት

አቢሲኒያ የጥራት ሽልማት አሰጣጥ መርሐ ግብር 

በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የኮፈሌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከ117 ሺህ ኩንታል በላይ ዘር መሰብሰቡን አስታወቀ

የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቡሹራ መሐመድ እንዳስታወቁት፣ ጽ/ቤቱ በ2014/15 የምርት ዘመን በባሌ እና አርሲ ዞኖች ከባለሀብቶች እና የግብርና ኮሌጆች በኮንትራት ማዕቀፍ 120 ሺህ ኩንታል ዘር ለማምረት አቅዶ፣ ከ117 ሺህ ኩንታል በላይ ማግኘት ተችሏል ብለዋል፡፡

ይህም የእቅዱን 97.5 ከመቶ ነው ያሉት አቶ ቡሹራ፣ የተሰበሰበው ምርት በጽ/ቤቱ ታሪክ ከፍተኛው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከተሰበሰበው ዘር ውስጥም ከ10 በላይ የስንዴ እና ገብስ ዝርያዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የተሰበሰበውን ዘር ኮፈሌ ከተማ በሚገኘው የማበጠሪያ ማሽን በማበጠርና በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፣ እስከ መጋቢት 12 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ከ50 ሺህ ኩንታል በላይ ዘር አበጥረው ማዘጋጀታቸውን እና ቀሪው በአጭር ጊዜ ተዘጋጅቶ ለአርሶ አደሩ እንደሚሰራጭ አብራርተዋል፡፡  አቶ ቡሹራ በቀጣይም የምርጥ ዘር አቅርቦትን ለማሳደግ ሌሎች ተጨማሪ ባለሀብቶች ከኮርፖሬሽኑ ጋር በጋራ ዘር እንዲያባዙ  ለማድረግ ማነጋገራቸውንና ከባለሀብቶቹም አዎንታዊ ምላሽ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡ የኮፈሌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በ2014/15 የምርት ዘመን ከኮርፖሬሽኑ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች መካከል በምርጥ ዘር ብዜት ከፍተኛ ምርት በመሰብሰብ ቀዳሚ ሲሆን፣ በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ደረጃ 117 ሺህ ኩንታል ምርት ሲሰበሰብ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ደረጃ እስከ አሁን ከተሰበሰበው ከ265 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ውስጥ 105 ሺህ 173 ኩንታል ተበጥሮ ተዘጋጅቷል።

                         ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በመንግሥት ከተሰጠው ሰፊ ተልዕኮ አንጻር የበርካታ ቋሚ ኮሚቴዎች ድጋፍ እንደሚያስፈልገው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ገለጹ፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ዶክተር ኢንጂነር መሐመድ አብዶ ይህንን የገለጹት፣ ኮርፖሬሽኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአዳማና በአዲስ አበባ ከተሞች ከመጋቢት 8-9/2015 ዓ.ም. ድረስ ባዘጋጀው የውይይትና የጉብኝት መርሐ ግብር ማጠቃለያ ነው፡፡

ኮርፖሬሽኑ ግብርናን ለማዘመን እያከናወናቸው ለሚገኘው ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ቋሚ ኮሚቴው በቀጣይ ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር የኮርፖሬሽኑ ሥራዎች የሚመለከታቸው ሌሎች ቋሚ ኮሚቴዎች ተቋሙን ማገዝ እንደሚጠበቅባቸው ፕሮፌሰር መሐመድ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ አኳያም የኮርፖሬሽኑን ልማት ለመደገፍና ከአቅም በላይ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች የሚገኙበት የጋራ የውይይት መድረክ እንደሚዘጋጅ አስታውቀዋል፡፡ በአዳማ ሂል ሳይድ ሆቴል የተካሄደውን የውይይት መድረክ የመሩት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ኮሬ በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ በተደረገላቸው ገለጻ ኮርፖሬሽኑ በግብርናው ዘርፍ መጠነ ሰፊ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተገንዝበዋል፡፡

አክለውም ኮርፖሬሽኑ ሲቋቋም የተፈቀደለትን ካፒታል በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ማሟላት መቻሉን እና በየዓመቱ እያተረፈ የሚሄድ ተቋም መሆኑን መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ ለሀገሪቷ የምጣኔ ሀብት እድገት እያበረከተ ያለው አስተዋጽዖ እና ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ የሚያከናውናቸው የድጋፍ ሥራዎች አበረታች ናቸው ያሉት ምክትል ሰብሳቢው፣ በቀጣይ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡ኮርፖሬሽኑ በበርካታ የሥራ መስኮች አፈጻጸም ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ፣ የመስኖ ልማት እና የእርሻ መሬት በማስፋፋት ወደ ውጭ የሚላኩ ሰብሎችን ለማምረት የጀመረውን እንቅስቃሴ አበረታተዋል፡፡ በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው ለኮርፖሬሽኑ ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀው፣ ከምርምር ተቋማትና ከአጋር ድርጅቶች ጋር የሚያደርገውን ግንኘነት አጠናክሮ እንዲቀጥል አስተያየት ሰጥተዋል፡ከተደረገላቸው ገለጻና በአካል ከተመለከቷቸው የሥራ እንቅስቃሴዎች በመነሳት “ኮርፖሬሽኑ ከተሰጠው ተልዕኮ አንጻር የሚገባውን ያህል ትኩረት አላገኘም” ያሉት የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው፣ ኮርፖሬሽኑ የኢትዮጵያን አርሶ አደር አቅፎ የያዘ ተቋም መሆኑን ተረድተናል ብለዋል፡፡አያይዘውም የተቋሙ ስትራተጂክ ዕቅድ ከሀገሪቷ የ10 ዓመት የግብርና ዘርፍ መሪ ዕቅድ ጋር ተጣጥሞ መዘጋጀቱ ለቀጣይ ስኬት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለተግባራዊነቱም ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

የደን ውጤቶችን (ሙጫ፣ እጣን፣ ከርቤና አበክድ) ለመሰብሰብና ወደ ውጭ ለመላክ የሚደረገው እንቅስቃሴ መጠናከር እንዳለበት፤ የግብርና ግብዓት አቅርቦትን ማስፋት እንደሚገባ፤ የማዳበሪያ ፋብሪካ በሀገር ውስጥ ማቋቋም እንደሚያስፈልግ፤ ለኦርጋኒክ ማዳበሪያ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት እንዲሁም የእርሻና የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች የቴክኒክ ማሠልጠኛ ማዕከልን በአዳዲስ የሥልጠና ማቴሪያሎች ማጠናከር እንደሚገባ የጠቆሙት የቋሚ ኮሚቴው አባላት፣  ኮርፖሬሽኑ ግብርናን ለማዘመን ያከናወናቸውን ሥራዎች በማድነቅ የተቋሙን የሥራ ኃላፊዎች አበረታተዋል፡፡የኮርፖሬሽኑን አጠቃላይ ገጽታ እና የልማት ሥራዎች ለቋሚ ኮሚቴው ገለጻ ያደረጉት የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም፣ በተለይም ከካፒታል ማሳደግ፣ ከአፈር ማዳበሪያ ግዥ ሥርዓት ደንብ ማውጣት፣ ለማዳበሪያ ግዥ የሚሆን ተዘዋዋሪ ፈንድ/Revolving fund ፈቃድ ከማግኘት እንዲሁም ከታክስ ጋር በተያያዘ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲቻል የቋሚ ኮሚቴውን ድጋፍ ጠይቀዋል፡፡

 የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባዘጋጀው የውይይትና የጉብኝት መርሐ ግብር ላይ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢ፣ ሦስት የንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ 19 አባላት እና ሰባት የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ባለሞያዎች ተገኝተዋል፡፡

           ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው፡፡

በኮርፖሬሽኑ የባህር ዳር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከ859 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን ማሰራጨቱን ገለጸ

አቶ እርቄ ገላው
በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የባህር ዳር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፡- በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የባህር ዳር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከ859 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን ለተጠቃሚዎች ማሰራጨቱን አስታወቀ፡፡
ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የ2015 በጀት ዓመት የሰባት ወራት የሥራ አፈጻጸሙን አስመልክቶ ለኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን የሥራ ክፍል በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ የቅባት እህሎችን ዘር ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ የውጭ ምንዛሬን ለማስገኘት እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፣ በተለይም አኩሪ አተር ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል። እስካሁንም 6 ሺህ 880 ኩንታል አኩሪ አተር መሰብሰቡን አስታውቋል፡፡
የመስኖ ልማትን ታሳቢ በማድረግም 2 ሺህ 100 ኩንታል ዘር መዘጋጀቱንና የተዘጋጀው ዘርም በውጭ ሀገር የዘር ጥራት ተቆጣጣሪ አካላት ጥራቱ እንዲረጋገጥ መደረጉን ገልጿል፡፡
ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ባለፉት ሰባት ወራት ከ859 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን ምርጥ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያ እና አግሮኬሚካሎችን ለጎንደር፣ ጎጃም፣ አዊ እና ሌሎችም አካባቢዎች ተደራሽ አድርጓል፡፡
በዚህም 7 ሺህ 356 ኩንታል ምርጥ ዘር፣ 282 ሺህ 583 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ፣ 13 ሺህ 59 ሊትር እና 500 ኪ.ግ ዱቄት አግሮኬሚካል ለምዕራብ አማራ አካባቢዎች ማሰራጨቱን በመግለጫው ጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ በ2014/15 የመኸር ወቅት በመንግሥት ዩኒቨርሲቲ፣ በሰፋፊ ባለሀብት እርሻዎች እና በአርሶ አደር ማሳዎች በ1 ሺህ 490 ሄክታር መሬት የበቆሎ፣ ስንዴ እና አኩሪ አተር ሰብል ምርጥ ዘሮችን ማባዛቱን እና እስከ ጥር 26 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ 18 ሺህ 334 ኩንታል ዘር ተሰብስቦ ወደ መጋዘን መግባቱን አስታውቋል፡፡
የዘር ብዜት ሥራን ከ882 አርሶ አደሮች፣ ከአንድ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ እና ከ13 የግል ባለሀብቶች ጋር በጋራ ማከናወኑንም በመግለጫው አንስቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ20 በላይ የተለያዩ ዝርያዎችን የማስተዋወቅ ሰርቶ ማሳያ መካሄዱን ከጽ/ቤቱ መግለጫ ለመረዳት ተችሏል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በዘንድሮ የመኸር ምርት ዘመን እስካሁን 195 ሺህ ኩንታል የተሻሻለ የምርጥ ዘር መሰብሰቡን ገለጸ

አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 20 ቀን 2015፡- በ2014/15 የመኸር ምርት ዘመን እስካሁን 195 ሺህ ኩንታል የተሻሻለ ምርጥ ዘር መሰብሰቡን የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ገለጸ።

ኮርፖሬሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በ2014/15 የመኸር የምርት ዘመን ምርት ለመሰብሰብ በያዘው ዕቅድ መሰረት የመሰብሰብ ሥራውን እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።

በምርት ዘመኑ 338 ሺህ ኩንታል ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙን ጠቅሶ፣ እስካሁን 195 ሺህ ኩንታል በመሰብሰብ እያጓጓዘ መሆኑን ገልጿል።

ኮርፖሬሽኑ በራሱና በኮንትራት የምርጥ ዘር ልማት መሸፈን ከቻለው ከ15 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ ወደ መጋዘኖች እያስገባ መሆኑንም ጠቁሟል።

በዚህም በኮፈሌ ቅርንጫፍ በምዕራብ አርሲ እና በባሌ ዞኖች በግብርና ኮሌጆች እና በሰፋፊ የግል ባለሀብት እርሻ በ5 ሺህ 427 ሄክታር መሬት ላይ ያባዛውን ዘር መሰብሰቡን ገልጿል።

በኮርፖሬሽኑ የኮፈሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ቡሹራ መሐመድ፣ ከአርዳይታና አጋርፋ የግብርና ኮሌጆች በተጨማሪ በባሌ ዞኖች በባለሀብቶች እርሻ ሦስት የገብስና 10 ዓይነት የስንዴ ዝርያዎችን በማባዛት የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ የማጓጓዝ ሥራ እየተካሄደ ነው ብለዋል።

እስከ ጥር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ምርት የመሰብሰብ ሥራ 50 በመቶ መከናወኑን እና 52 ሺህ ኩንታል ምርት ተረክበው ወደ ኮርፖሬሽኑ መጋዘኖች መጓጓዛቸውን ገልጸዋል።

በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ የዘር ጥራት ክትትልና ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ጋሩማ ገመዳ፣ የምርት ጥራትን ለማስጠበቅ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ የምርት መሰብሰብ ሥራ እየተፋጠነ ይገኛል ብለዋል።

በምርጥ ዘር ብዜት በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶችም፣ የአርሶ አደሩ ምርታማነትን በማሳደግ በቂ የምርጥ ዘር አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግ ጥራቱን የጠበቀ ምርት እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ በተቀናጀ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት የአርሶ አደሮች፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እና የግል ባለሀብቶችን የምርጥ ዘር ሰብል በተመጣጣኝ ዋጋ የመሰብሰብና የማጓጓዝ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ለኢዜአ በላከው መግለጫ ላይ ጠቅሷል።

በዚህም መሰረት እስከ ጥር 17 ድረስ ለአርሶ አደሮች፣ ለልማት ድርጅቶችና ባለሀብቶች 146 ሺህ ኩንታል ምርት መሰብሰቡን አስታውቋል። ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ አካባቢዎች ባሉት የራሱ እና የኮንትራት እርሻዎች የ21 የሰብል ዓይነቶች 70 ዝርያዎችን በማባዛትና በማዘጋጀት ለአርሶ አደሮች እያቀረበ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።