(አዲስ አበባ፣ ጥር 10 ቀን 2016 ዓ.ም፣ ግብርና ሚኒስቴር) የግብርና ሚኒስትሩ ዶ/ር ግርማ አመንቴ እና የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትሩ ዶ/ር ዓለሙ ስሜ በ2016/17 ምርት ዘመን የአፈር ማደበሪያ አገባብ ዕቅድ ክንውን ላይ የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ በተያዘው የምርት ዘመን የግብርና ሚኒስቴር 23 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት አቅዶ ከክልሎች በተሰበሰበው የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት መሰረት 19.4 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት 930 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ተድርጎ ግዥ እየተፈጸመ መሆኑን ዶ/ር ግርማ አመንቴ ተናግረዋል፡፡ ግዥ ከተፈፀመው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥም 5 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ ገብቷል ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡ በምርት ዘመኑም ከሚገዛው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 25 በመቶው ለመስኖ ስንዴ ልማት፣ 20 በመቶው ለበልግ እርሻ ስራ እንዲሁም ቀሪው 55 በመቶ ለመኸር እርሻ ጥቅም ላይ እንደሚውል አብራርተዋል፡፡ አርሶና አርብቶ አደሩም የሚቀርብለትን የአፈር ማዳበሪያ በአግባቡ በመጠቀም የግብርና ልማት ስራዎችን እንዲያከናውኑ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ የአፈር ማዳበሪያ የማጓጓዙን ስራ ለማከናወን ከ10 ሺህ በላይ የየብስ ተሸከርካሪዎችን በማሰማራት እየተሰራ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ከ16 በላይ የባቡር ማጓጓዣዎችንም በመጠቀም ወደብ የደረሰውን የአፈር ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ የማስገባት ስራ እየተሰራ መሆኑን ዶ/ር ዓለሙ ጠቁመዋል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም የ2016/17 በጀት ዓመት የአፈር ማደበሪያ አገባብ ዕቅድ እና ክንውን ላይ የስትሪንግ ኮሚቴ ውይይት ተካሂዷል፡፡
ካሜራ፡- ያሬድ አሰፋ
ዘጋቢ፥- ሰለሞን ደምሰው