ኮርፖሬሽኑ በአዲስ አበባ ያስገነባውን የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤት አስመረቀ
* በሌላ ዜና ለኮርፖሬሽኑ የውስጥ አገልግሎት የሚውሉ የዳቦ መጋገሪያ እና የጉድጓድ ውኃ ፕሮጀክቶች ተመርቀዋል
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፡- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በአዲስ አበባ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ያስገነባውን የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤት ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም አስመረቀ። ወይዘሮ አስናቀች ፀጋ ለተባሉ የወረዳ 6 ነዋሪ ከ1 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባውን መኖሪያ ቤት በመመረቅ ቁልፍ የአስረከቡት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም እና በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የወረዳ 6 አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቶፊቅ ከድር ናቸው። በዚሁ ወቅት ንግግር የአደረጉት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ ኮርፖሬሽኑ የሕዝብ ተቋም እንደመሆኑ ለሕዝብ ያለውን አጋርነት ለማረጋገጥ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ ይገኛል ብለዋል። ኮርፖሬሽኑ ባለፉት ዓመታት ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል በመፍጠር እና ከሚያገኘው ትርፍ ላይ በየዓመቱ ለማኅበራዊ ኃላፊነት በጀት በመመደብ በተለያዩ አካባቢዎች ለበርካታ ማኅበረሰቦች የገንዘብ እና የቁሳቁስ ድጋፎችን ሲያደርግ መቆየቱን አቶ ክፍሌ አብራርተዋል፡፡ አክለውም ኮርፖሬሽኑ በ2016 በጀት ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብርን ከማስቀጠል ባሻገር ለተለያዩ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ከ16 ሚሊየን ብር በላይ ማውጣቱን ጠቁመው፣ ከአከናወናቸው ሥራዎች አንዱ የወይዘሮ አስናቀች ፀጋ መኖሪያ ቤት ግንባታ መሆኑን አስታውቀዋል። የወረዳ 6 አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ቶፊቅ ከድር በበኩላቸው፣ ከኮርፖሬሽኑ ጋር በመተባበር በርካታ ሰው ተኮር የሆኑ ሥራዎችን እያከናወኑ እንደሚገኙ ጠቁመው፣ ኮርፖሬሽኑ የአስገነባው የአስፋልት መንገድ፣ አጥር እና ሌሎች የግቢ ማስዋብ ሥራዎች የአካባቢውን ገጽታ በተሻለ መልኩ መቀየራቸውን ተናግረዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ አርሶ አደሩን ብቻ ሳይሆን የከተማ ነዋሪዎችንም ጭምር ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ቶፊቅ፣ የአቅመ ደካማ ቤት እድሳት ሥራ፣ የውኃ እና ጎርፍ ማፋሰሻ ተግባራት ለዚህ ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል፡፡ በዚህ የተነሳም የአካባቢው ነዋሪ ኮርፖሬሽኑን እንደ እራሱ ንብረት እያየው ይገኛል ብለዋል። በኮርፖሬሽኑ የውስጥ አቅም የተገነባው የወይዘሮ አስናቀች መኖሪያ ቤት በብሎኬት የተሰራ ሲሆን፣ የቀድሞውን እድሜ ጠገብ አሮጌ ቤት አፍርሶ ለመገንባት የሦስት ወራት ጊዜ ወስዷል፡፡ 7መኖሪያ ቤቱ ማብሰያ ቤትን ጨምሮ አራት ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ የቤት ውስጥ ቁሳቁስ ተሟልቶለታል፡፡ በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያ ኮርፖሬሽኑ በ2016 በጀት ዓመት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ለአበረከተው የልማት አስተዋጽዖ ከክፍለ ከተማው የምስጋና የምስክር ወረቀት ተበርክቶለታል። በሌላ ዜና ለኮርፖሬሽኑ የውስጥ አገልግሎት የሚውሉ የዳቦ መጋገሪያ እና የጉድጓድ ውኃ ፕሮጀክቶች ሐምሌ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ተመርቀዋል። የውኃ ፕሮጀክቱ በተደጋጋሚ ያጋጥም የነበረን የውኃ እጥረት ያቃለለ ሲሆን፣ ዳቦ ቤቱ ደግሞ ለኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል። በቀጣይም ለአካባቢው ማኅበረሰብ ዳቦ እና እንቁላል ለማቅረብ ታስቧል።
ግብርናን ከማዘመን ጎን ለጎን ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ለሕዝብ ያለንን አጋርነት እናረጋግጣለን!