ለመተሃራ ስኳር ፋብሪካ 700 ሄክታር የሸንኮራ አገዳ ማሳ እያዘጋጀ ይገኛል
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 23/2016 ዓ.ም. (ኢግሥኮ)፡- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የአርሶ አደሮችን፣ በግብርና ሥራ የተሰማሩ ባለሀብቶችን እና የተለያዩ ድርጅቶችን የደረሰ ሰብል በተመጣጣኝ ዋጋ እየሰበሰበ ነው፡፡በኮርፖሬሽኑ የእርሻ መሣሪያዎች እና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መንግሥቱ ክፍሌ እንደገለጹት፣ ኮርፖሬሽኑ ከጥቅምት 2016 ዓ.ም አጋማሽ ጀምሮ በሞጆ እና ሄረሮ ዙሪያ ለሚገኙ አርሶ አደሮች እና ባለሀብቶች የሰብል መሰብሰብ ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡የሀገሪቱ የግብርና ምርት ሙሉ በሙሉ እስኪሰበሰብ ድረስ ኮርፖሬሽኑ አገልግሎቱን እንደሚቀጥል የተናገሩት አቶ መንግሥቱ፣ ከቀጣዩ ሳምንት ጀምሮ በጎጃም የአየሁ እርሻ ልማት የደረሰ ሰብል እንደሚሰበሰብ ተናግረዋል፡፡እንደ ሥራ አስፈጻሚው ማብራሪያ፣ ኮርፖሬሽኑ በ10 አጭዶ መውቂያ መሣሪያዎች የሰብል መሰብሰብ አገልግሎት እየሰጠ ሲሆን፣ አገልግሎቱን ለማጠናከር ተጨማሪ 10 አጭዶ መውቂያዎችን ከውጭ አስመጥቶአል።

አቶ መንግሥቱ ክፍሌ

በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ የመተሃራ ስኳር ፋብሪካን ነባር የሸንኮራ አገዳ በማስወገድ ለአዲስ የሸንኮራ አገዳ ተከላ 700 ሄክታር መሬት እያዘጋጀ መሆኑን አቶ መንግሥቱ አክለው አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በክልሎች ካሉት 25 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ውስጥ የሞጆ፣ ሄረሮ እና ቡሬ ጣቢያዎች በዋናነት የተቀናጀ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ለማስፋፋት እና ለማጠናከር የተቋቋሙ ናቸው፡፡