አቶ እርቄ ገላው
በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የባህር ዳር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ

አዲስ አበባ፣ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፡- በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የባህር ዳር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከ859 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን የግብርና ምርት ማሳደጊያ ግብዓቶችን ለተጠቃሚዎች ማሰራጨቱን አስታወቀ፡፡
ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ የ2015 በጀት ዓመት የሰባት ወራት የሥራ አፈጻጸሙን አስመልክቶ ለኮርፖሬት ኮሚዩኒኬሽን የሥራ ክፍል በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ የቅባት እህሎችን ዘር ወደ ውጭ ሀገራት በመላክ የውጭ ምንዛሬን ለማስገኘት እየተንቀሳቀሰ ሲሆን፣ በተለይም አኩሪ አተር ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል። እስካሁንም 6 ሺህ 880 ኩንታል አኩሪ አተር መሰብሰቡን አስታውቋል፡፡
የመስኖ ልማትን ታሳቢ በማድረግም 2 ሺህ 100 ኩንታል ዘር መዘጋጀቱንና የተዘጋጀው ዘርም በውጭ ሀገር የዘር ጥራት ተቆጣጣሪ አካላት ጥራቱ እንዲረጋገጥ መደረጉን ገልጿል፡፡
ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ባለፉት ሰባት ወራት ከ859 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን ምርጥ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያ እና አግሮኬሚካሎችን ለጎንደር፣ ጎጃም፣ አዊ እና ሌሎችም አካባቢዎች ተደራሽ አድርጓል፡፡
በዚህም 7 ሺህ 356 ኩንታል ምርጥ ዘር፣ 282 ሺህ 583 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ፣ 13 ሺህ 59 ሊትር እና 500 ኪ.ግ ዱቄት አግሮኬሚካል ለምዕራብ አማራ አካባቢዎች ማሰራጨቱን በመግለጫው ጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ በ2014/15 የመኸር ወቅት በመንግሥት ዩኒቨርሲቲ፣ በሰፋፊ ባለሀብት እርሻዎች እና በአርሶ አደር ማሳዎች በ1 ሺህ 490 ሄክታር መሬት የበቆሎ፣ ስንዴ እና አኩሪ አተር ሰብል ምርጥ ዘሮችን ማባዛቱን እና እስከ ጥር 26 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ 18 ሺህ 334 ኩንታል ዘር ተሰብስቦ ወደ መጋዘን መግባቱን አስታውቋል፡፡
የዘር ብዜት ሥራን ከ882 አርሶ አደሮች፣ ከአንድ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ እና ከ13 የግል ባለሀብቶች ጋር በጋራ ማከናወኑንም በመግለጫው አንስቷል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከ20 በላይ የተለያዩ ዝርያዎችን የማስተዋወቅ ሰርቶ ማሳያ መካሄዱን ከጽ/ቤቱ መግለጫ ለመረዳት ተችሏል፡፡