የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከሠራተኛ ማኅበር አመራሮችና ከመላ ሠራተኞች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 21/2018 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፡- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከተቋሙ የሠራተኛ ማኅበር አመራሮችና ከመላ ሠራተኞች ጋር መስከረም 21/2018 ዓ.ም ተወያዩ።
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወይዘሮ የሺእመቤት ነጋሽ በዛሬው ዕለት በኮርፖሬሽኑ ዋና መ/ቤት በተዘጋጁ ሁለት የትውውቅና የውይይት መድረኮች ላይ ባስተላለፉት መልእክት፣ ኮርፖሬሽኑን ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ከሠራተኛ ማኅበር አመራሮች እንዲሁም ከመላ ሠራተኞች ጋር ተቀራርበው በጋራ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
በመተማመንና ተቀራርቦ በመሥራት እንደሚያምኑ የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ ኮርፖሬሽኑ የሚጠበቅበትን ሀገራዊ ተልዕኮ እንዲያሳካ የተቋሙ የሥራ አመራርና ሠራተኞች በከፍተኛ የሥራ ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት በጋራ መረባረብ ይገባቸዋል ብለዋል። አክለውም በግብርናው ዘርፍ ለኮርፖሬሽኑ ከተሰጠው ከፍተኛ ሀገራዊ ኃላፊነት አኳያ የተጀመሩና አዳዲስ ሥራዎች በውጤት ታጅበው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡
“የኮርፖሬሽኑን የቀድሞ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያምን እንደ አባት ነው የምናያቸው” በሚል ከሠራተኛው ለቀረበው አስተያየት፣ ወይዘሮ የሺእመቤት በሰጡት ምላሽ፣ “ከተሰጠኝ ኃላፊነት ባሻገር እኔም እንደ እናት ሆኜ ላገለግላችሁ ቃል እገባለሁ።” ብለዋል።
የኮርፖሬሽኑ የመሠረታዊ የሠራተኛ ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ብርሃኑ ደበሌ በበኩላቸው፣ “አንድ ተቋም ጤናማና ውጤታማ የሚሆነው ሥራ አመራሩና የሠራተኛ ማኅበሩ በመግባባትና በትብብር ሲሠሩ ነው።” ካሉ በኋላ እንደከዚህ ቀደም ጊዜያት ሁሉ ለኮርፖሬሽኑ ቀጣይ ስኬት ማኅበሩና ሠራተኛው ከሥራ አመራሩ ጋር በመግባባትና በቅርበት ለመሥራት ዛሬም ዝግጁ መሆናቸውን በማኅበሩ ስም አረጋግጠዋል።
በውይይቱ ወቅት ከሠራተኞች ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ወይዘሮ የሺእመቤት ነጋሽ ምላሽ ሰጥተዋል።





















































