ስለ እኛ
ምስረታ
የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢግሥኮ) በግብርናው ዘርፍ ከ30 እስከ 40 ዓመት ድረስ በተናጠል አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩ አምስት ነባር ድርጅቶችን (የኢትዮጵያ ምርጥ ዘር ድርጅት፣ የግብርና ምርት ማሳደጊያዎች አቅራቢ ድርጅት፣ የእርሻ መሣሪያዎችና የቴክኒክ አገልግሎት አክሲዮን ማኅበር፣ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ድርጅት እና የተፈጥሮ ሙጫ ምርትና ገበያ ድርጅት) በማዋሃድ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 368/2008 መሠረት ታህሳስ 2008 ዓ.ም የተቋቋመ መንግሥታዊ የልማት ድርጅት ነው፡፡
ተጠሪነት
በግሉ ዘርፍና በተደራጁ ማኅበራት የማይሸፈኑ የገበያ ክፍተቶች ውስጥ የድርሻውን በመውሰድ ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ላይ የሚገኘው ኮርፖሬሽኑ ተጠሪነቱ ለኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ሲሆን፣ በሥራ አመራር ቦርድ ይመራል፡፡
የተቋቋመበት ዓላማ
የተቋቋመበት ዓላማ ለግብርና ምርትና ምርታማነት ዕድገት አስተዋጽዖ የሚያደርጉ እና ለዘመናዊ እርሻና ለአግሮ ኢንዱስትሪ መስፋፋት መሠረት የሚሆኑ ቴክኖሎጂዎችን እና ግብዓቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ተደራሽ በማድረግ ሀገራዊ ልማትና ዕድገትን ለማፋጠን ነው፡፡
አደረጃጀት
የአርሶ አደሩ እና አርብቶ አደሩ አለኝታ የሆነው ኮርፖሬሽኑ በመንግሥት የተሰጠውን ተልዕኮ ከመወጣት አኳያ በሦስት ኮርፖሬት ዘርፎች፣ ዓላማ አስፈፃሚ በሆኑ አምስት የኦፕሬሽን ዘርፎች፣ በ15 ድጋፍ ሰጪ የሥራ ሂደቶች እንዲሁም በበርካታ ቅርንጫፎች እና በጣቢያዎች በተደራጀ መዋቅር በ1,397 ቋሚና በ250 ኮንትራት በድምሩ በ1,647 ሠራተኞች ግብርናን ለማዘመን እየሰራ ይገኛል፡፡
የአንድ መስኮት አገልግሎት
የአንድ መስኮት የተቀናጀ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው ኮርፖሬሽኑ፣ በተቀናጀ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ከመሬት ዝግጅት እስከ ጎተራ የሚዘልቁ የግብርና ሥራዎችን ያከናውናል፡፡ በተጨማሪም ለግብርና መዘመንና ለምርታማነት እድገት የላቀ አስተዋጽዖ ያላቸውን ግብዓቶች (ምርጥ ዘር፣ ጠጣርና ፈሳሽ ማዳበሪያዎች፣ አግሮኬሚካሎች) እንዲሁም የእርሻ መሣሪያዎችን ከእነተቀጽላቸው እና መለዋወጫቸው በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚዎች ያቀርባል፡፡
ከዚህ ባሻገር ኮርፖሬሽኑ ለደንበኞቹ እየሰጠ የሚገኘውን የአንድ መስኮት አገልግሎት የተሟላ ለማድረግ የምክር፣ የቴክኒክና ሞያ ሥልጠና፣ የዘር ብጠራ፣ የደረቅ ጭነት ትራንስፖርት እና የተሽከርካሪዎች ጥገና አገልግሎቶችን በዋና መ/ቤት እና በቅርንጫፎች ተደራሽ በማድረግ ላይ ነው።
ምርጥ ዘር
በሀገር ደረጃ በምርጥ ዘር አቅርቦት ፋና ወጊ የሆነው ኮርፖሬሽኑ፣ በተለያዩ ክልሎች የራሱን ስድስት የምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት ጣቢያዎችን በማቋቋም እንዲሁም በሰፋፊ የመንግሥትና የግል እርሻዎች እና በክላስተር በተደራጁ አርሶ አደሮች ማሳ በኮንትራት በመስራት በአጠቃላይ ከ20 ሺህ ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ የ22 ሰብሎችን 90 ዝርያዎች እያባዛ በዓመት ከ400 ሺህ ኩንታል በላይ ዘር ለተጠቃሚዎች እያቀረበ ይገኛል፡፡ ይህም በሀገር ደረጃ ካለው የምርጥ ዘር ፍላጎት ውስጥ 30 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ እንዲያሟላ አስችሎታል፡፡
በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ ክልሎች በአገኛቸው ተጨማሪ የእርሻ መሬቶች ዘር እያባዛ ሲሆን፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ሰብሎችን ለማምረትም ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
የደን ውጤቶች
ኮርፖሬሽኑ የደን ውጤቶች የሆኑትን ሙጫ፣ እጣን፣ ከርቤና አበከድ በማምረት እና በግዥ በማሰባሰብ አበጥሮ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ገበያ ጭምር በማቅረብ በዓመት በሚሊየን የሚቆጠር የውጭ ምንዛሪ በማስገኘት ላይ ነው፡፡
ተቋሙ እነዚህን ምርቶች የሚሰበስበው በዘርፉ ከተሰማሩ ማኅበራትና ግለሰቦች በግዥ መልክ ሲሆን፣ የደን ውጤቶቹ በአብዛኛው በትግራይ፣ በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በኦሮሚያ እና በሶማሌ ክልሎች ቆላማ አካባቢዎች ይገኛሉ፡፡
ማዳበሪያ፣ አግሮኬሚካልና የእንስሳት መድኃኒት
ኮርፖሬሽኑ በሀገር ውስጥ ብቸኛ የጠጣር የአፈር ማዳበሪያ አስመጪ ሲሆን፣ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያዎች (በጠጣርና በፈሳሽ መልክ)፣ ጸረ አረም፣ ጸረ ነፍሳትና ጸረ ፈንገስ ኬሚካሎች እና የእንስሳት መድኃኒቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚዎች በማቅረብ ላይ ነው፡፡
የእርሻ መሣሪያዎች
ኮርፖሬሽኑ ለሀገሪቱ መልክአ ምድር እና የአየር ንብረት ተስማሚ የሆኑ ዘመናዊና ጥራት ያላቸውን ትራክተሮችና ተቀጽላዎች/implements – ማረሻ፣ መከስከሻ፣ መስመር ማውጫ፣ ዘር መዝሪያ፣ ማዳበሪያ መበተኛ…/፣ ኮምባይን ሀርቨስተር እንዲሁም የኮንስትራክሽን እና የኬሚካል መርጫ መሣሪያዎችና መለዋወጫዎችን ያቀርባል።
የሜካናይዜሽን አገልግሎት
የተቀናጀ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎትን በሁሉም የሀገሪቷ አካባቢዎች ተደራሽ በማድረግ የሚታወቀው ኮርፖሬሽኑ በግብርናው ዘርፍ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች፣ ከፊል አርብቶ አደሮች፣ ባለሃብቶች፣ የልማት ድርጅቶች ወዘተ ከመሬት ዝግጅት እስከ ጎተራ የሚዘልቁ የግብርና ሥራዎችን ያከናውናል፡፡
የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና የሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል
ኮርፖሬሽኑ ለካፒታል ፕሮጀክት በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት የዘር ማበጠሪያና የሜካናይዜሽን አገልግሎት ተደራሽ ባልሆነባቸው ክልሎች የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና የሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል ለማቋቋም እየሰራ ነው፡፡ ለአብነት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በቦንጋ ከተማ የአስገነባውን ግዙፍ ማዕከል መጥቀስ ይቻላል፡፡ በተመሳሳይ ይህን መሰል ማዕከል በሌሎች ክልሎችም ለማስፋፋት የሚያስችል እንቅስቃሴ እየተደረገ ነው፡፡
የእርሻ መሣሪያዎችን የመገጣጠም ሥራ
የግብርና ሜካናይዜሽንን በማስፋፋት ረገድ ኮርፖሬሽኑ አዳዲስ የእርሻ መሣሪያዎችን ታዋቂ ከሆኑ የአውሮፓ እና የቻይና አምራች ኩባንያዎች በማስመጣት እና ባለው ወርክሾፕ በሂደት ሙሉ በሙሉ ገጣጥሞ ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ ከውጭ ኩባንያዎች ጋር በሽርክና መስራት የሚችልበትን ስምምነት እያደረገ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ተቋሙ የእርሻ መሣሪያዎችን በከፊል የመገጣጠም ሥራ እያከናወነ ይገኛል፡፡
የደረቅ ጭነት ትራንስፖርት እና የተሽከርካሪዎች ጥገና አገልግሎቶች
ኮርፖሬሽኑ ከባድ ተሽከርካሪዎችን በማሰማራት ለውስጥ እና ለውጭ ደንበኞች የግብርና ግብዓቶችን እና የእርሻ መሣሪያዎችን እንዲሁም ሌሎች የደረቅ ጭነቶችን የማጓጓዝ አገልግሎት ይሰጣል፡፡
በሌላ በኩል ለውስጥ እንዲሁም ለተለያዩ የግልና የመንግሥት ተቋማት ደንበኞች የተሽከርካሪዎች የቅድመ መከላከል እና የብልሽት ጥገና አገልግሎት ይሰጣል፡፡
በተጨማሪም ለከባድ እና ቀላል ተሽከርካሪዎች ዓመታዊ የቴክኒክ ብቃት ማረጋገጫ ምርመራ/ቦሎ/ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
የዓመታዊ ሽያጭ፣ ትርፍና የተፈቀደ ካፒታል እድገት
ኮርፖሬሽኑ ባለፉት ዓመታት በሀገራዊ የግብርና ዘርፍ የ10 ዓመት መሪ ዕቅድ እና ለሦስተኛ ጊዜ በአዘጋጀው የተቋሙ ስትራተጂክ ዕቅድ (ከ2016-2020 ዓ.ም) እየተመራ ውጤትን መሰረት ያደረገ የዕቅድ አፈጻጸም ምዘና ሥርዓትን (BSC) የለውጥ መሣሪያ አድርጎ ወደ ሥራ በመግባቱ፣ በየዓመቱ የሂሳብ መግለጫ በIFRS ደረጃዎች መሰረት በወቅቱ ሂሳብ በመዝጋቱና በማስቀጠሉ እንዲሁም የISO 9001፡2015 የጥራት ሥራ አመራር ሥርዓትን በመተግበሩ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ ችሏል፡፡
በዚህም ዓመታዊ ገቢውን ሲቋቋም ከነበረበት ከ1.4 ቢሊዮን ብር ወደ 10.12 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ከታክስ በፊት ትርፉን ከ45.6 ሚሊዮን ብር ወደ 1.8 ቢሊዮን ብር ማሳደግ ችሏል፡፡ ከዚህ የተነሳ ኮርፖሬሽኑ በየዓመቱ ምርቱን እያሳደገ እና አገልግሎቶቹን ይበልጥ ተደራሽ እያደረገ በመቀጠሉ እንዲሁም ትርፋማ ሆኖ በመዝለቁ ምክንያት ሲቋቋም በመንግሥት የተፈቀደለትን 2.44 ቢሊዮን ብር ካፒታል በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በማሟላት አሁን ላይ የተፈቀደ ካፒታሉን ወደ 7 ቢሊዮን 564 ሚሊዮን ብር ማሳደግ ችሏል፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያውን ተከትሎም የተቋሙን ካፒታል በድጋሚ ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ነው፡፡
ማኅበራዊ ኃላፊነት
ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድም ኮርፖሬሽኑ በየዓመቱ በአማካይ ለ2500 ዜጎች ጊዜያዊ የሥራ እድል የሚፈጥር ሲሆን፣ ከሚያገኘው የተጣራ ትርፍ ላይም በየዓመቱ ለማኅበራዊ አገልግሎት በጀት በመመደብ በምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት አካባቢዎች ለሚገኘው ማኅበረሰብ እና በሀገር አቀፍ ደረጃ በመንግሥት ለሚቀርብለት የተለያዩ የድጋፍ ጥሪዎች እና የስፖንሰርሺፕ ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ሲሰጥ ቆይቷል፤ አሁንም አቅም በፈቀደ መጠን ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡
በዚህም በበጎ አድራጎት ሥራዎች በእርሻ ልማቱ አካባቢዎች ለሚገኘው ማኅበረሰብ ትምህርት ቤት በመገንባት፣ መብራት በማስገባት፣ የአቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤቶች በማደስ፣ ለችግረኛ ቤተሰብ ልጆች የትምህርት መርጃ መሣሪያዎችን በመስጠት፣ ችግኞችን በመትከል እና ደም በመለገስ ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡ በተመሳሳይ ለአካባቢው አርሶ አደሮች በአምስት በመቶ የዋጋ ቅናሽ ምርጥ ዘር በማቅረብ ለአርሶ አደሩ ያለውን አለኝታነት በማረጋገጥ ላይ ይገኛል፡፡
እውቅና እና ሽልማት
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢግሥኮ) በጥራትና በተመጣጣኝ ዋጋ በሚያቀርባቸው የግብርና ግብዓቶችና በሚሰጣቸው የተቀናጁ አገልግሎቶች በገበያ ውስጥ ተመራጭ ስለመሆኑ የረጅም ዓመት ደንበኞቹ ምስክሮች ናቸው፡፡
ኮርፖሬሽኑ በግብርናው መስክ በአስመዘገበው አበረታች ውጤት የአቢሲኒያ ዓለም አቀፍ የጥራት ድርጅት ለመጀመሪያ ጊዜ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለኢንደስትሪ ሽልማት ካጫቸው ከ57 ሺህ በላይ አምራች እና አገልግሎት ሰጪ የመንግሥት፣ የግል እና ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ውስጥ ከተመረጡ 50 ተቋማት አንዱ በመሆን መጋቢት 2015 ዓ.ም የመጀመሪያውን የኢንደስትሪ የከፍተኛ ክብር ሽልማት ተቀዳጅቷል፡፡
በተጨማሪም ኮርፖሬሽኑ በ2016 በጀት ዓመት ከ743 ሚሊየን ብር በላይ ግብር በመክፈል ለሁለተኛ ጊዜ በታማኝ ግብር ከፋይነት በፕላቲነም ደረጃ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እጅ ሽልማት ተቀብሏል፡፡
ከዚህ ባሻገር በ2015/16 የምርት ዘመን በሀገር አቀፍ ደረጃ በስንዴ ልማት ከሀገራዊ ፍላጎት እስከ ውጭ ገበያ አቅራቢነት በመሸጋገር ሂደት ለአበረከተው የላቀ አስተዋጽዖ እንዲሁም በ2016/17 ምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ ግዥ፣ አቅርቦት እና ሥርጭት እንዲሳለጥ ለተወጣው ከፍተኛ ድርሻም የእውቅናና የምስጋና የምስክር ወረቀት እና ዋንጫ አግኝቷል፡፡
በሌላ በኩል የኮርፖሬሽኑ የወንዶች የመረብ ኳስ ቡድን የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) በ2015 ዓ.ም በአዘጋጀው የስፖርት ውድድር ሻምፒዮን በመሆን ዋንጫ ተቀብሏል።
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!