
* “የኮርፖሬሽኑ የ2016 በጀት ዓመት የሂሳብ ሪፖርት ነቀፌታ የሌለበት (Unqualified Audit Opinion/Clean Audit Report) በመሆኑ የተቋሙ ማኔጅመንት ሊመሰገን ይገባል።” የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ
አዲስ አበባ፣ ጥር 12/2017 ዓ.ም (ኢግሥኮ):- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም አበረታች መሆኑን የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ ገለጸ። በግብርና ሚኒስቴር የስብሰባ አዳራሽ ጥር 12 ቀን 2017 ዓ.ም የተገመገመው የኮርፖሬሽኑ የመጀመሪያ ስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም በአራቱ የውጤት ተኮር እይታዎች ሲመዘን አበረታች እንደሆነ የቦርድ ሰብሳቢው ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
የኮርፖሬሽኑ የ2016 በጀት ዓመት ሂሳብ ሪፖርትን በተመለከተም፣ ሂሳቡ በውጭ ኦዲተር ተመርምሮ ነቀፌታ የሌለበት የኦዲት አስተያየት የተሰጠበት በመሆኑ የተቋሙ ማኔጅመንት ሊመሰገን ይገባል ብለዋል። ሰብሳቢው አክለውም ኮርፖሬሽኑ ከ2013 በጀት ዓመት ጀምሮ በሂሳብ እና በኦዲት አፈጻጸም ያሳየው ከፍተኛ ለውጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ከውጭ እያስመጣ በስፋት የማስተዋወቅ እና ለገበያ የማቅረብ ሥራዎችን በስፋት አጠናክሮ እንዲቀጥል ቦርዱ የሥራ መመሪያ ሰጥቶአል። በተለይም የበቆሎ መፈልፈያ ማሽኖችን (Maize Combine Harvesters) ወደ ሀገር ውስጥ በብዛት በማስገባት የአርሶ አደሮችን እና የባለሃብቶችን ፍላጎት ለማሟላት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የካፒታል ፕሮጀክቶች ክትትል እና አፈጻጸም ላይ ለውጥ እንዳለ የጠቆሙት የቦርድ ሰብሳቢው ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት እና በጥራት አጠናቆ ወደ አዳዲስ ፕሮጀክቶች መሸጋገር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
በመጨረሻም የበጀት ዓመቱን ዕቅድ በቀጣይ ስድስት ወራት ሙሉ በሙሉ በመተግበር ገቢን ማሳደግ ይገባል ብለዋል።







ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!