አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፡-የአፈር ማዳበሪያን በወቅቱ ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ በሚያስችል አሠራር ላይ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከአፈር ማዳበሪያ አቅራቢዎች ጋር ጥቅምት 22 ቀን 2017 ዓ.ም በኮርፖሬሽኑ ዋና መስሪያ ቤት ውይይት አደረገ፡፡
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም፣ የውይይት መድረኩ ዓላማ በአፈር ማዳበሪያ ግዥ፣ ጨረታ፣ ትራንስፖርት እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይቶ የጋራ መፍትሔ ማስቀመጥ መሆኑን አስረድተዋል።
በወቅቱ ከአፈር ማዳበሪያ አቅራቢዎች ለተነሱ ጥያቄዎች፣ አስተያየቶች እና ምክረ አሳቦች የኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ወልደአብ ደምሴ እና አቶ ክፍሌ ወልደማርያም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የተሰጡ አስተያየቶችን እና ግብረ መልሶችን እንደ ግብዓት በመውሰድ የአፈር ማዳበሪያ አቅራቢዎችን ተሳትፎ ሊገድቡ የሚችሉ ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ እንደሚደረግ አቶ ወልደአብ ተናግረዋል፡፡
አቅራቢዎቹ በበኩላቸው፣ ኮርፖሬሽኑ ከአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ጋር በተያያዘ የውይይት መድረክ ማዘጋጀቱ እና መመካከሩ የሚደነቅ ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከግብርና ሚኒስቴር በየዓመቱ በሚቀርብለት ሀገራዊ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት መነሻ መሰረት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ዓለም አቀፍ ጨረታ በማውጣት የአፈር ማዳበሪያ ግዥን በመፈጸም ለተጠቃሚዎች እያቀረበ የሚገኝ የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው፡፡
###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!