አዲስ አበባ፣ ህዳር 11/ 2016 ዓ.ም. (ኢግሥኮ)፡- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከቻይና ያስመጣቸውን ‘ዙምላየን’ በመባል የሚታወቁ 10 አጭዶ መውቂያዎችን (combine harvesters) ዛሬ ህዳር 11 ቀን 2016 ተረከበ፡፡ የአጭዶ መውቂያዎቹን ቁልፍ የዙምላየን ካምፓኒ ተወካይ ሚስተር አሊን ኪን ለኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም አስረክበዋል፡፡
በርክክቡ ወቅት አቶ ክፍሌ እንደተናገሩት፣ የቻይና የእርሻ እና የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች አምራች ኩባንያ ከሆነው ዙምላየን ጋር ኮርፖሬሽኑ የንግድ ስምምነት በመፈጸም ለመጀመሪያ ጊዜ አጭዶ መውቂያ መሣሪያዎችን ለአርሶ አደሮች፣ በግብርና ሥራ ለተሰማሩ ድርጅቶች እና ባለሀብቶች ማቅረቡን ገልጸዋል። አጭዶ መውቂያዎቹ ብልሽት ሲያጋጥማቸው በቀላሉ የሚጠገኑ፣ ለአያያዝና አጠቃቀም ምቹ እና ለሀገራችን የአየር ንበረትና የመሬት አቀማመጥ ተስማሚ በመሆናቸው በአብዛኛው ተጠቃሚዎች ዘንድ ተመራጭነት እንደሚኖራቸው አቶ ክፍሌ አስታውቀዋል፡፡
የዙምላየን ተወካይ አሊን ኪን በበኩላቸው፣ አጭዶ መውቂያዎቹን ለማስተዋወቅ በመገኘታቸው ክብር እንደሚሰማቸው ጠቁመው፣ ዙምላየን ኩባንያ በቻይና ግንባር ቀደም የኮንስትራክሽን እና እርሻ መሣሪያዎች አምራች መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ኩባንያቸው የእርሻ መሣሪያዎችን በማቅረብ ረገድ የስኬት ታሪክ ያለው መሆኑን አንስተው፣ ከኮርፖሬሽኑ ጋር ከሽያጭ በኋላ በተለያዩ የቴክኒክ እና ሞያ ድጋፎች አብረው እንደሚሰሩና በዚህም ስኬታማ እንደሚሆኑ አስረድተዋል፡፡ በሌላ በኩል አጭዶ መውቂያዎቹ በምርት መሰብሰብ ወቅት የሚከሰት ብክነትን በማስቀረት ምርታማነትን እንደሚጨምሩም ተናግረዋል፡፡ ከርክክቡ ቀጥሎ የአጭዶ መውቂያዎቹ የትውውቅ ፕሮግራም የተካሄደ ሲሆን፤ አጭዶ መውቂያው ስንዴ፣ በቆሎ፣ ጤፍ፣ አኩሪ አተር እና ሌሎች የሰብል አይነቶችን ማጨድና መውቃት እንደሚችል በባለሞያዎች ተብራርቷል። በአንድ ጊዜ እስከ አራት ሜትር ስፋት ያለው ሰብል አጭዶ መውቃት እንደሚችል የተነገረለት ዙምላየን አጭዶ መውቂያ፣ 25 ኩንታል የመያዝ አቅም ያለው ጎተራ/ቋት እንዳለው በትውውቁ ላይ ተገልጿል። በዋናው መሪያ ቤት ግቢ በተካሄደው የርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ ከዙምላየን የመጡ የቴክኒክ ባለሞያዎች፣ የኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ አባል፣ የሥራ መሪዎች፣ የመሠረታዊ የሠራተኛ ማኅበር ሰብሳቢ እና ሠራተኞች ተገኝተዋል፡፡ ከዙምላየን የመጡ የቴክኒክ ባለሞያዎች ከህዳር 7-8/2016 ዓ.ም ስለ አጭዶ መውቂያው ለኮርፖሬሽኑ ኦፕሬተሮችና መካኒኮች የቴክኒክ ሞያ ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የግብርና ግብዓቶችን እና የእርሻ መሣሪያዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለተጠቃሚዎች በማቅረብ፣ ከማሳ ዝግጅት እስከ ጎተራ የሚዘልቅ የተቀናጀ የሜካናይዜሽን አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን በማስተዋወቅ የሀገሪቷን ግብርና ለማዘመን እየሰራ ይገኛል። ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት የቼክ ሪፐብሊክ ስሪት የሆነውን ‘ዜቶር’ ትራክተር እና ሌሎች የእርሻ መሣሪያዎችን ከአውሮፓ እና ቻይና በማስመጣት ለተጠቃሚዎች በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡