አዲስ አበባ (ኢዜአ) ጥር 20 ቀን 2015፡- በ2014/15 የመኸር ምርት ዘመን እስካሁን 195 ሺህ ኩንታል የተሻሻለ ምርጥ ዘር መሰብሰቡን የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ገለጸ።
ኮርፖሬሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በ2014/15 የመኸር የምርት ዘመን ምርት ለመሰብሰብ በያዘው ዕቅድ መሰረት የመሰብሰብ ሥራውን እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።
በምርት ዘመኑ 338 ሺህ ኩንታል ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙን ጠቅሶ፣ እስካሁን 195 ሺህ ኩንታል በመሰብሰብ እያጓጓዘ መሆኑን ገልጿል።
ኮርፖሬሽኑ በራሱና በኮንትራት የምርጥ ዘር ልማት መሸፈን ከቻለው ከ15 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ ወደ መጋዘኖች እያስገባ መሆኑንም ጠቁሟል።
በዚህም በኮፈሌ ቅርንጫፍ በምዕራብ አርሲ እና በባሌ ዞኖች በግብርና ኮሌጆች እና በሰፋፊ የግል ባለሀብት እርሻ በ5 ሺህ 427 ሄክታር መሬት ላይ ያባዛውን ዘር መሰብሰቡን ገልጿል።
በኮርፖሬሽኑ የኮፈሌ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ቡሹራ መሐመድ፣ ከአርዳይታና አጋርፋ የግብርና ኮሌጆች በተጨማሪ በባሌ ዞኖች በባለሀብቶች እርሻ ሦስት የገብስና 10 ዓይነት የስንዴ ዝርያዎችን በማባዛት የደረሱ ሰብሎችን በመሰብሰብ የማጓጓዝ ሥራ እየተካሄደ ነው ብለዋል።
እስከ ጥር 16 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ምርት የመሰብሰብ ሥራ 50 በመቶ መከናወኑን እና 52 ሺህ ኩንታል ምርት ተረክበው ወደ ኮርፖሬሽኑ መጋዘኖች መጓጓዛቸውን ገልጸዋል።
በቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱ የዘር ጥራት ክትትልና ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ጋሩማ ገመዳ፣ የምርት ጥራትን ለማስጠበቅ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ የምርት መሰብሰብ ሥራ እየተፋጠነ ይገኛል ብለዋል።
በምርጥ ዘር ብዜት በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩ ባለሀብቶችም፣ የአርሶ አደሩ ምርታማነትን በማሳደግ በቂ የምርጥ ዘር አቅርቦት እንዲኖር ለማድረግ ጥራቱን የጠበቀ ምርት እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ በተቀናጀ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት የአርሶ አደሮች፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች እና የግል ባለሀብቶችን የምርጥ ዘር ሰብል በተመጣጣኝ ዋጋ የመሰብሰብና የማጓጓዝ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ለኢዜአ በላከው መግለጫ ላይ ጠቅሷል።
በዚህም መሰረት እስከ ጥር 17 ድረስ ለአርሶ አደሮች፣ ለልማት ድርጅቶችና ባለሀብቶች 146 ሺህ ኩንታል ምርት መሰብሰቡን አስታውቋል። ኮርፖሬሽኑ በተለያዩ አካባቢዎች ባሉት የራሱ እና የኮንትራት እርሻዎች የ21 የሰብል ዓይነቶች 70 ዝርያዎችን በማባዛትና በማዘጋጀት ለአርሶ አደሮች እያቀረበ እንደሚገኝም ተጠቁሟል።