* የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ላይ ዘንድሮ የታየው አፈጻጸምም ጥሩ ነው ተብሏል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 28/2016 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፡- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በመንግሥት የተሰጠውን ተልዕኮ እየተወጣ እና ትርፋማነቱን እያረጋገጠ በመዝለቁ ሊበረታታ እንደሚገባ በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡
ይህ የተገለጸው የኮርፖሬሽኑ የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ግንቦት 28 ቀን 2016 ዓ.ም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በቀረበበት ወቅት ነው።
በዚሁ ወቅት የቋሚ ኮሚቴው የአገልግሎት ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ኢያሱ ሳላ እንደገለጹት፣ ኮርፖሬሽኑ በመላ ሀገሪቱ ምርትና አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግ ከሚያከናውነው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ ባሻገር ማኅበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት ቀጣይነት ያለው ትርፍ እያረጋገጠ መሄዱ የሚያበረታታ ተግባር ነው ብለዋል።
ሰብሳቢው አክለውም ኮርፖሬሽኑ በዘጠኝ ወራት ያሳካቸውን የልማት ሥራዎች እንዲያስጠብቅ እንዲሁም የተጀመሩ ሥራዎችን በማሳካት እድገቱን እንዲያስቀጥል አሳስበዋል።
የፕሮጀክት አተገባበርን አስመልክተው በሰጡት አስተያየትም፣ ተቋሙ ለፕሮጀክት አፈጻጸም መሻሻል ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት ተናግረዋል።የቋሚ ኮሚቴው የኢንዱስትሪ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ አዲስ ዓለማየሁ በበኩላቸው፣ የኮርፖሬሽኑን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም አድንቀው፣ ኮርፖሬሽኑ ምክር ቤቱ ድጋፍ እንዲያደርግለት ከጠየቃቸው ጉዳዮች ውስጥ አብዛኛዎቹ ላይ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል። ይሁንና ተሰብሳቢ ሒሳብ ላይ ግን ኮርፖሬሽኑ እራሱ ማስፈጸም እንዳለበት አስገንዝበዋል።የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ላይ ዘንድሮ የታየው አፈጻጸም ጥሩ ነው ያሉት ወ/ሮ አዲስ፣ ከዚህ ቀደም ማዳበሪያ ከውጭ ለማስገባት የሚያጋጥሙ የኤልሲ፣ የግዥ እና የሥርጭት ተግዳሮቶች አሁን ላይ እንደተፈቱ መረዳታቸውን ጠቁመዋል፡፡አስተያየታቸውን ሲያጠቃልሉም፣ የደን ውጤቶችን (ሙጫ፣ ዕጣን፣ ከርቤና አበከድ) ለመሰብሰብና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚደረገው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
በዕለቱ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም የተቋሙን አሁናዊ ቁመና፤ የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም፤ የ2013፣ 2014 እና 2015 በጀት ዓመታት ነቀፌታ የሌላቸው የኦዲት ግኝቶች (Unqualified audit opinion)፤ የፕሮጀክቶችና ካፒታል ግዥዎች ዕቅድ አፈጻጸም እንዲሁም ድጋፍና ክትትል የሚሹ ጉዳዮችን በሪፖርት መልክ ለቋሚ ኮሚቴው አቅርበዋል።በመጨረሻም በቋሚ ኮሚቴው ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ምላሽ ሰጥተዋል።
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!