ኮርፖሬሽኑ በሀገር ደረጃ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነውን የምርጥ ዘር ፍላጎት እያቀረበ እንደሚገኝ የገለጹት በኮርፖሬሽኑ የኢትዮጵያ የምርጥ ዘር አቅርቦት እና የደን ውጤቶች አቅርቦት ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘነበ ወልደሥላሴ፣ በምርት ዘመኑ የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የሚያስችሉ ሥራዎች በመከናወን ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በአሁኑ ወቅት ኮርፖሬሽኑ  68 በመቶ የሚሆነውን ምርጥ ዘር በሰፋፊ የመንግሥት እና ባለሀብት እርሻዎች እና በአርሶ አደር ማሳ፣ ቀሪውን 32 በመቶ ደግሞ በራሱ የምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት ጣቢያዎች በማባዛት ለተጠቃሚዎች እያቀረበ እንደሚገኝም ጠቁመዋል፡፡

በቀጣይ የምርጥ ዘር ጥራትና አቅርቦትን የበለጠ ለማሳደግ እንፈልጋለን ያሉት አቶ ዘነበ፣ “ለዚህም የራስ እርሻ መሬት ከፍተኛ ፋይዳ ስላለው የእርሻ መሬቶችን በማፈላለግ ተጨማሪ አዳዲስ የምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት ጣቢያዎችን ለማቋቋም እየሰራን እንገኛለን” ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኮርፖሬሽኑ በ2013/14 የምርት ዘመን ከ14 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ በዘር በመሸፈን 281 ሺህ 852 ኩንታል ምርት መሰብሰብ የቻለ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 137 ሺህ 217 ኩንታል ዘር ለተጠቃሚዎች አቅርቧል።

በአሁኑ ወቅት ዘግይተው የሚዘሩ እንደ ጤፍ የመሳሰሉ ዘሮች ሽያጭ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት አቶ ዘነበ፣ ቀሪው ዘር ለመጠባበቂያ እንዲሆን መከማቸቱን ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ዘነበ ገለጻ፣ ምርጥ ዘር የግብርና ምርትን ከ50 በመቶ በላይ የሚያሳድግ ዋነኛ ግብዓት በመሆኑ፤ ኮርፖሬሽኑ የ22 የሰብል ዓይነቶችን 69 ዝርያዎች በማባዛት እና በማዘጋጀት ለአርሶ አደሩ፣ ለከፊል አርሶ አደሩ፣ ለአርሶ አደር ማኅበራት፣ ለሰፋፊ እርሻዎች፣ ለክልል ግብርና ቢሮዎች፣ ለእርዳታ ድርጅቶች እንዲሁም ለሌሎች ዘር ተጠቃሚዎች እያቀረበ ይገኛል ብለዋል፡፡

ኮርፖሬሽኑ የዘር ብዜት ክፍተቶችን ለመሙላት በማሰብ ሌሎች ዘር አባዥዎች አዋጭ ባለመሆናቸው ምክንያት የማያባዟቸውን ቅድመ መስራች እና መስራች ዘሮችን በማባዛት እያቀረበ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል በሀገራችን አንዳንድ አካባቢዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተፈጠረ የጸጥታ ችግር ምክንያት ምርጥ ዘር ማባዛት አለመቻሉን የጠቆሙት አቶ ዘነበ፣ ይህንን ለማካካስ ኮርፖሬሽኑ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ካፋ ዞን ታማሻሎ በሚባል አካባቢ የተረከበውን የምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ መሬት ወደ ሥራ በማስገባት ምርጥ ዘር ማባዛት መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

” እንደ ተቋም በሀገር ደረጃ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነውን የምርጥ ዘር ፍላጎት እያቀረብን እንገኛለን” ያሉት አቶ ዘነበ፣ ኮርፖሬሽኑ  68 በመቶ የሚሆነውን ዘር በሰፋፊ የመንግሥት እና ባለሀብት እርሻዎች እና በአርሶ አደር ማሳ ላይ፣ ቀሪውን 32 በመቶ ደግሞ በራሱ የምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት ጣቢያዎች በማባዛት እያቀረበ እንደሚገኝ አብራርተዋል፡፡

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከሚያከናውናቸው በርካታ የግብርና ልማት ሥራዎች ውስጥ አንዱ የተለያዩ የአዝርዕት፣ አትክልት እና ፍራፍሬ ምርጥ ዘር ማባዛት፣ ማዘጋጀት እና ማሰራጨት ነው፡፡

በኮርፖሬሽኑ ስር የሚገኘው የኢትዮጵያ የምርጥ ዘር አቅርቦት እና የደን ውጤቶች አቅርቦት ዘርፍ ከ40 ዓመታት በላይ ምርጥ ዘር የማባዛት፣ የማዘጋጀት እና የማሰራጨት ልምድ አለው፡፡