አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 24/2016 ዓ.ም (ኢግሥኮ):- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የ2016 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ጥሩ መሆኑን የተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ አስታወቀ።
በግብርና ሚኒስቴር የስብሰባ አዳራሽ ሚያዝያ 24 ቀን 2016 ዓ.ም የተገመገመው የኮርፖሬሽኑ የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም በአራቱ የውጤት ተኮር እይታዎች ሲመዘን ጥሩ እንደሆነ የቦርድ ሰብሳቢው ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
ሰብሳቢው በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ከኮርፖሬሽኑ የተሻለ ውጤት እንደሚጠበቅ ገልጸው፣ በእነዚህ ጊዜያት የግብርና ግብዓቶችን በተሟላ ሁኔታ ለአርሶ አደሩ እና በግብርናው ዘርፍ ለተሰማሩ አካላት ለማቅረብ የቅርብ ክትትል ያስፈልጋል ብለዋል።
ቀጣዩ ጊዜ በግብርናው ዘርፍ ወቅታዊ ሥራዎች የሚከናወኑበት ወሳኝ ወቅት ነው ያሉት ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፣ ይህንን ለማሳካት ኮርፖሬሽኑ ከክልሎች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመስራት በዘርፉ እንደ ሀገር የተያዙ ዕቅዶችን መፈጸም እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።
ለዚህም ኮርፖሬሽኑ በዘጠኝ ወራት በከፊል የፈጸማቸውን የተወሰኑ ሥራዎች በቀጣዮቹ ሁለት ወራት ሙሉ በመሉ ለመተግበር ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ በአጽንዖት ተናግረዋል።
አክለውም የኮርፖሬሽኑ ማኔጅመንት የነገን ዛሬ ላይ በመስራት ተቋሙን በሁሉም የሥራ ዘርፎች ውጤታማ እና በገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ነው ያሳሰቡት።በመጨረሻም ተቋሙ የኤክስፖርት አቅሙን ለማሳደግ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙ ምርቶች ላይ የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አበክረው አስገንዝበዋል።
በዕለቱ ከሥራ አመራር ቦርድ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶች የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም እና የማኔጅመንት አባላት ምላሽ ሰጥተዋል።
###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!