ግብርናን ለማዘመን እየሰራ የሚገኘው የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢግሥኮ) ከተቋቋመበት ከታህሳስ 2008 ዓ.ም ጀምሮ ከመሬት ዝግጅት እስከ ጎተራ የሚዘልቅ የተቀናጀ የሜካናይዜሽን አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።
ከዚህ በተጨማሪ ምርታማነትን የሚያሳድጉ የግብርና ግብዓቶችን እንዲሁም የእርሻ መሣሪያዎችን ከእነተቀጽላቸው እና መለዋወጫቸው ጋር በተመጣጣኝ ዋጋ ለደንበኞቹ በማቅረብ ላይ ነው።
በሌላ በኩል የእርሻ መሣሪያዎችን በከፊል በመገጣጠም፣ ዘር በማበጠር፣ የደረቅ ጭነት ትራንስፖርት በማመቻቸት እና ከሽያጭ በኋላ የቴክኒክና ሞያ፣ የምክርና የጥገና አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ የደንበኞቹን ፍላጎት ለማርካት እየተጋ የሚገኝ ተቋም ነው።
ኮርፖሬሽኑ የተፈጥሮ ሙጫ ምርቶችን ለውጭ ገበያ በማቅረብ የሚያገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለእርሻ መሣሪያዎች እና መለዋወጫዎች ግዥ መደጎሚያነትም ያውላል፡፡ኢግሥኮ ባለፉት ስምንት ዓመታት ተልእኮውን ለመወጣት በአደረገው ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ ችሏል።
በዚህም በየዓመቱ ገቢውን በማሳደግ ትርፋማ የሆነ የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው።
በኦፕሬሽን ሥራዎች በግሉ ዘርፍና በተደራጁ ማኅበራት የማይሸፈኑ የገበያ ክፍተቶች ውስጥ የድርሻውን በማበርከት ላይ የሚገኘው ኮርፖሬሽኑ፣ ዓመታዊ ሽያጩን ሲቋቋም ከነበረበት 1.4 ቢሊዮን ብር በ2015 በጀት ዓመት ከ11.2 ቢሊዮን ብር በላይ ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡
በተመሳሳይ ከታክስ በፊት ያለውን ትርፍ ከ45.6 ሚሊዮን ብር ወደ 1.5 ቢሊዮን ብር አሳድጓል፡፡
ይህ በመሆኑም ሲቋቋም በመንግሥት የተፈቀደለትን 2.44 ቢሊዮን ብር ካፒታል በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ በማሟላት አሁን ላይ ካፒታሉን ወደ 7 ቢሊዮን 564 ሚሊዮን ብር አድርሷል፡፡
በአጠቃላይ የአርሶና አርብቶ አደሩ አለኝታ የሆነው የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢግሥኮ) በአንድ መስኮት የተቀናጀ የሜካናይዜሽን አገልግሎት በመስጠት እንዲሁም ምርጥ ዘር፣ ጠጣርና ፈሳሽ ማዳበሪያዎች፣ አግሮኬሚካሎች፣ የእንስሳት መድሃኒት እና እርሻ መሣሪያዎች በማቅረብ ግብርናን ለማዘመን ከሚያደርገው ከፍተኛ ጥረት በተጨማሪ ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ በሕዝብ ዘንድ ይታወቃል።