አርዳይታ፣ ህዳር3/2016 ዓ.ም (ኢግሥኮ):- በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የአርዳይታ ቅድመ መስራች፣ መስራች እና የተመሰከረለት ዘር እርሻ ልማት የደረሰ ምርት የመሰብሰብ ሥራን የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አስጀመሩ። ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ክፍሌ ወልደማርያም ዛሬ ህዳር 3 ቀን 2016 ዓ.ም በአርዳይታ የዘር ማባዣ እርሻ ልማት ተገኝተው የምርት መሰብሰብ ሥራን አስጀምረዋል። የእርሻ ጣቢያው በ2015/16 የምርት ዘመን የስንዴ፣ ገብስ፣ ጎመን ዘር እና በቆሎ ሰብሎች 20 ዝርያዎችን ማባዛቱን የገለጹት አቶ ክፍሌ፣ በቅድመ መስራች፣ መስራች እና የተመሰከረለት ዘር ከተሸፈነው 3 ሺህ 69.32 ሄክታር መሬት ከ82 ሺህ ኩንታል በላይ ዘር እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል። ከሚሰበሰበው ዘር ውስጥ ለበጋ መስኖ ልማት የሚውል የስንዴ ዘር ዋነኛው መሆኑንም አክለው ተናግረዋል። በሀገር ደረጃ በምርጥ ዘር አቅርቦት ፋና ወጊ የሆነው የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በተለያዩ ክልሎች አምስት አካባቢዎች የቅድመ መስራች፣ መስራች እና የተመሰከረለት ዘር ማባዣ እርሻ ልማት ጣቢያዎችን (አርዳይታ፣ ጎንዴ ኢተያ፣ ጊቤ፣ ቻግኒ እና ታማሻሎ) በማቋቋም እንዲሁም በሰፋፊ የመንግሥትና የግል እርሻዎች እና በክላስተር በተደራጁ አርሶ አደሮች ማሳዎች በኮንትራት በመስራት በአማካይ በ15 ሺህ ሄክታር መሬት የ22 ሰብሎችን 78 ዝርያዎች እያባዛ በዓመት ከ350 ሺህ ኩንታል በላይ ዘር ለተጠቃሚዎች እያቀረበ ይገኛል፡፡ ይህም ኮርፖሬሽኑ በሀገር ደረጃ ካለው የምርጥ ዘር ፍላጎት ውስጥ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነውን ድርሻ እንዲያሟላ አስችሎታል፡፡ ኮርፖሬሽኑ በ2015/16 ምርት ዘመን በሦስት የዘር ደረጃዎች በእራሱ የምርጥ ዘር ማባዣ እርሻዎች፣ በሰፋፊ ኮንትራት አባዥዎች እና በክላስተር በተደራጁ አርሶ አደሮች ማሳዎች በዘር ከሸፈነው 20 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት 473 ሺህ 791 ኩንታል ዘር ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል። የሀገሪቷን ግብርና ለማዘመን በአንድ መስኮት የተሟላ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው ኮርፖሬሽኑ፣ የተለያዩ የግብርና ግብዓቶችንና የእርሻ መሣሪያዎችን ለተጠቃሚዎች ከማቅረቡ ባሻገር የተቀናጀ የግብርና ሜካናይዜሽን፣ የደረቅ ጭነት እንዲሁም ከሽያጭ በኋላ የቴክኒክና ሞያ፣ የምክርና የጥገና አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ ላይ ይገኛል።