አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29/2016 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፡- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከአውሮፓ ካስመጣቸው ‘ዜቶር’ ትራክተሮች ውስጥ ስምንት ትራክተሮችን ከእነተቀጽላቸው ‘ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ’ በመባል ለሚታወቅ ድርጅት በሽያጭ አስረከበ፡፡ ድርጅቱ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ስምንት ትራክተሮችን፣ ስምንት ማረሻዎችን፣ ሦስት መከስከሻዎችን እና ሦስት መስመር ማውጫዎችን ከኮርፖሬሽኑ ገዝቷል።  ዛሬ ጥቅምት 29 ቀን 2016 ዓ.ም በኮርፖሬሽኑ ዋና መስሪያ ቤት በተካሄደ የርክክብ ሥነ ሥርዓት ላይ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም ለፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍስሀ እሸቱ (ዶ/ር) የትራክተሮቹን ቁልፍ አስረክበዋል፡፡

አቶ ክፍሌ በሥነ ሥርዓቱ ወቅት ይፋ እንዳደረጉት፣ በቀጣይ ለአማራ ክልል የ75 ዜቶር ትራክተሮች ርክክብ እንደሚደረግ ይጠበቃል። ኮርፖሬሽኑ የሀገሪቷን ግብርና ለማዘመን ጥራት ያላቸውን አስተማማኝ የእርሻ መሣሪያዎች ከአውሮፓና ከቻይና እያስመጣ ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ እያቀረበ ይገኛል ያሉት አቶ ክፍሌ፣ ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ የተረከባቸው የቼክ ሪፐብሊክ ስሪት የሆኑት ዜቶር ትራክተሮች የግብርና ምርታማነትን እንደሚያሳድጉ አስታውቀዋል፡፡ አክለውም ኮርፖሬሽኑ ለገበያ ለሚያቀርባቸው ዜቶር ትራክተሮች እና ሌሎች የእርሻ መሣሪያዎች ከሽያጭ በኋላ በዋናው መ/ቤት እና በክልሎች ባሉት 25 ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የጥገና አገልግሎት እንደሚሰጥ እና መለዋወጫዎች እንደሚያቀርብ  አረጋግጠዋል። የፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍስሀ እሸቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው ድርጅታቸው ከኮርፖሬሽኑ ጋር ዘርፈ ብዙ የሥራ ግንኙነት እንዳለው ጠቁመው፣ በምርጥ ዘር ብዜት ከኮርፖሬሽኑ ጋር በጋራ እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ኮርፖሬሽኑ ተደራሽ እና አስተማማኝ የሆነ አገልግሎት ስለሚሰጥ ትራክተሮቹን ከኮርፖሬሽኑ ለመግዛት እንደወሰኑ የገለጹት ፍስሀ እሸቱ (ዶ/ር)፣ በቀጣይም  ተጨማሪ ትራክተሮችን እንደሚገዙ ጠቁመዋል፡፡ በተመሳሳይ በመሬት ዝግጅት፣ በግብርና ግብዓት አቅርቦት እና በሌሎችም የዘርፉ አገልግሎቶች ከኮርፖሬሽኑ ጋር በትብብር መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ አያይዘው ገልጸዋል፡፡ ፐርፐዝ ብላክ ኢትዮጵያ በግብርና፣ በምግብ ማቀናበር፣ በሪል ስቴት፣ በችርቻሮ ንግድ እና በሌሎች መስኮች የተሰማራ ድርጅት ነው፡፡