ኮርፖሬሽኑ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኮንትራት እርሻ እያባዛ የሚገኘውን የድቃይ በቆሎ የተመሰከረለት የዘር ማሳ አስጎበኘ * የክልሉ መንግሥት ኮርፖሬሽኑ ላቀረበው ተጨማሪ የዘር ማባዣ መሬት ጥያቄ ምላሽ እንደሚሰጥ አስታውቋል ============================ አሶሳ፣ ጥቅምት 27/2016 ዓ.ም (ኢግሥኮ):- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በኮንትራት እርሻ ከባለሀብት ጋር እያባዛ የሚገኘውን የድቃይ በቆሎ የተመሰከረለት የዘር ማሳ ለክልል፣ ዞን፣ ወረዳ እና ቀበሌ አመራሮች ጥቅምት 27 ቀን 2016 ዓ.ም አስጎበኘ። ከክልሉ ዋና ከተማ አሶሳ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው የአሶሳ ዞን አብረሃሞ ወረዳ በተዘጋጀው የመስክ ጉብኝት እና በአሶሳ ከተማ ባምቡ ፓራዳይዝ ሆቴል በተካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ተወካይ አቶ አጥናፉ አጎናፍር ፣ የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ባበከር ሀላፋ፣ የግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አጥናፉ ባቡር እንዲሁም ሌሎች የቢሮ፣ የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ አመራሮች እና የግብርና ባለሞያዎች ተገኝተዋል። በእንግዶች የተጎበኘው BH 546 በመባል የሚጠራው የድቃይ በቆሎ የተመሰከረለት ዘር ማባዣ ማሳ ሲሆን፣ ኮርፖሬሽኑ አቶ ሞላ ተመስገን ከተባሉ ባለሀብት ጋር በ146 ሄክታር መሬት ላይ በጋራ እያለመ የሚገኘው የኮንትራት እርሻ ነው። ይህንን እርሻ ጨምሮ ኮርፖሬሽኑ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በእሶሳ ዞን አምስት አካባቢዎች በ328 ሄክታር መሬት ላይ ድቃይ በቆሎ እና ድቃይ ያልሆነ በቆሎ የተመሰከረለት ዘር እያባዛ እንደሚገኝ እና 12 ሺህ ኩንታል ዘር እንደሚጠበቅ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት ለኮርፖሬሽኑ የዘር ማባዣ 1500 ሄክታር መሬት መፍቀዱን ያስታወሱት አቶ ክፍሌ፣ በሀገሪቷ እና በክልሉ ካለው የዘር ፍላጎት አንጻር ተጨማሪ 3500 ሄክታር የዘር ማባዣ መሬት አሶሳ ዞን ላይ እንዲሰጣቸው የክልሉን መንግሥት ጠይቀዋል። “ተጨማሪ መሬት ካገኘን በክልሉ የግብርና ግብዓት አቅርቦት እና የሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከል እናቋቁማለን” ያሉት አቶ ክፍሌ፣ የማዕከሉ መቋቋም በክልሉ እና በአቅራቢያው የሚገኙ አርሶ አደሮች እና በግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች የግብርና ግብዓቶችን፣ የእርሻ መሣሪያዎችን እና መለዋወጫዎችን እንዲሁም የሜካናይዜሽን፣ የጥገና፣ የምክር እና የቴክኒክ ሞያ አገልግሎቶችን በቅርበት ለማግኘት እንደሚያስችላቸው አስረድተዋል። በኮርፖሬሽኑ ለቀረበው ተጨማሪ የዘር ማባዣ መሬት ጥያቄ የክልሉ መንግሥት ምላሽ እንደሚሰጥ የግብርና ቢሮ ኃላፊው አቶ ባበከር ሀላፋ አስታውቀዋል። በጉብኝቱ ላይ የተገኙት በአሶሳ ዞን የአብረሃሞ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ አቡዱላጢፍ አፉዲ፣ ኮርፖሬሽኑ በክልሉ ውስጥ የሚታየውን የዘር ችግር ለመቅረፍ የሚያደረገውን ጥረት አድንቀው፣ ልማቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል። አክለውም ኮርፖሬሽኑ ትራክተሮች እና የግብርና ግብዓቶችን በስፋት ካቀረበላቸው በወረዳ ደረጃ የተሻለ ውጤት እንደሚያመጡ ገልጸዋል። የመስክ ጉብኝቱ እና የውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፣ ኮርፖሬሽኑ በአዘጋጀው መርሀ ግብር ልምድ እንዳገኙ እና ስለ ኮርፖሬሽኑም የሥራ እንቅስቃሴ ግንዛቤ እንደጨበጡ ተናግረዋል። ኮርፖሬሽኑ በክልሉ ውስጥ የልማት እንቅስቃሴ ማካሄዱ የክልሉን ግብርና በማዘመን የአርሶ አደሩን የግብዓት ችግር ለመቅረፍ እንደሚረዳም አመልክተዋል። በመስክ ጉብኝቱ ወቅት ቴክኒካዊ ማብራሪያ የሰጡት አቶ በሊና ብርሃኑ በኮርፖሬሽኑ የነቀምት ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ እንዳስረዱት፣ BH 546 የድቃይ በቆሎ የተመሰከረለት ዘር ከነባር ዝርያዎች በተሻለ ከፍተኛ ምርት ከመስጠቱ ባሻገር በሽታን የመቋቋም አቅሙ ከፍተኛ ነው። የኮርፖሬሽኑን አጠቃላይ ገጽታ በተመለከተም የኮርፖሬት ኦፕሬሽን ዐቢይ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፈለቀ ገዛኸኝ ለተሳታፊዎች ገለጻ አድርገዋል። በወቅቱ በተሳታፊዎች ለቀረቡ ጥያቄዎችና አስተያየቶች የኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ በሀገር ደረጃ በምርጥ ዘር አቅርቦት ፋና ወጊ የሆነው የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ በተለያዩ ክልሎች የራሱን አምስት የምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት ጣቢያዎችን በማቋቋም እንዲሁም በሰፋፊ የመንግሥትና የግል እርሻዎች እና በክላስተር በተደራጁ አርሶ አደሮች ማሳ በኮንትራት በመስራት በአጠቃላይ በ15 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የ22 ሰብሎችን 78 ዝርያዎች እያባዛ በዓመት ከ350 ሺህ ኩንታል በላይ ዘር ለተጠቃሚዎች እያቀረበ ይገኛል፡፡ ይህም በሀገር ደረጃ ካለው የምርጥ ዘር ፍላጎት ውስጥ ከ30 በመቶ በላይ የሚሆነውን ድርሻ እንዲያሟላ አስችሎታል፡፡
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!