አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 22/2016 ዓ.ም. (ኢግሥኮ)፡- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከአውሮፓ ከሚያስመጣቸው 75 ትራክተሮች ውስጥ 59ኙን ተረከበ።

በኮርፖሬሽኑ የእርሻ መሣሪያዎች አቅርቦት፣ ማርኬቲንግና ሽያጭ መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጎሳዬ ቶሎሳ እንዳስታወቁት፣ ኮርፖሬሽኑ የሀገሪቷን ግብርና ለማዘመን የሚያስችሉ የእርሻ መሣሪያዎችን ከእነተቀጽላቸው ከአውሮፓ እና ከቻይና እያስመጣ ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

ኮርፖሬሽኑ ከ110 እስከ136 የፈረስ ጉልበት ያላቸውን  ‘ዜቶር’ በመባል የሚታወቁ ትራክተሮችን ከቼክ ሪፐብሊክ እያስመጣ መሆኑን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፣ ከታዘዙ 75 ትራክተሮች ውስጥ እስከአሁን 59ኙን መረከባቸውን አስታውቀዋል፡፡ ቀሪዎቹ 16 ትራክተሮችም በቅርቡ  ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡

ዜቶር ትራክተር ላይ የቴክኒክ ብልሽት ቢያጋጥም መለስተኛ የእጅ መሣሪያዎችን በመጠቀም በቀላሉ መጠገንና ማስተካከል እንደሚቻልም አስረድተዋል። ኮርፖሬሽኑ ትራክተሮችን ከማቅረብ ባሻገር ከሽያጭ በኋላ ለደንበኞች የቴክኒክና ሞያ ሥልጠና፣ የጥገና እና የምክር አገልግሎቶች አዲስ አበባ በሚገኘው የቴክኒክና ሞያ ማሠልጠኛ ማዕከል እና በቅርንጫፎቹ እየሰጠ ይገኛል፡፡