የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ዶክተር ኢንጂነር መሐመድ አብዶ ይህንን የገለጹት፣ ኮርፖሬሽኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በአዳማና በአዲስ አበባ ከተሞች ከመጋቢት 8-9/2015 ዓ.ም. ድረስ ባዘጋጀው የውይይትና የጉብኝት መርሐ ግብር ማጠቃለያ ነው፡፡
ኮርፖሬሽኑ ግብርናን ለማዘመን እያከናወናቸው ለሚገኘው ዘርፈ ብዙ ሥራዎች ቋሚ ኮሚቴው በቀጣይ ከሚያደርገው ድጋፍ ባሻገር የኮርፖሬሽኑ ሥራዎች የሚመለከታቸው ሌሎች ቋሚ ኮሚቴዎች ተቋሙን ማገዝ እንደሚጠበቅባቸው ፕሮፌሰር መሐመድ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ አኳያም የኮርፖሬሽኑን ልማት ለመደገፍና ከአቅም በላይ የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች የሚገኙበት የጋራ የውይይት መድረክ እንደሚዘጋጅ አስታውቀዋል፡፡ በአዳማ ሂል ሳይድ ሆቴል የተካሄደውን የውይይት መድረክ የመሩት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ ኮሬ በበኩላቸው እንደተናገሩት፣ በተደረገላቸው ገለጻ ኮርፖሬሽኑ በግብርናው ዘርፍ መጠነ ሰፊ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተገንዝበዋል፡፡
አክለውም ኮርፖሬሽኑ ሲቋቋም የተፈቀደለትን ካፒታል በአምስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ማሟላት መቻሉን እና በየዓመቱ እያተረፈ የሚሄድ ተቋም መሆኑን መረዳታቸውን ገልጸዋል፡፡በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ ለሀገሪቷ የምጣኔ ሀብት እድገት እያበረከተ ያለው አስተዋጽዖ እና ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ የሚያከናውናቸው የድጋፍ ሥራዎች አበረታች ናቸው ያሉት ምክትል ሰብሳቢው፣ በቀጣይ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል ብለዋል፡፡ኮርፖሬሽኑ በበርካታ የሥራ መስኮች አፈጻጸም ጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የገለጹት ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ፣ የመስኖ ልማት እና የእርሻ መሬት በማስፋፋት ወደ ውጭ የሚላኩ ሰብሎችን ለማምረት የጀመረውን እንቅስቃሴ አበረታተዋል፡፡ በመጨረሻም ቋሚ ኮሚቴው ለኮርፖሬሽኑ ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀው፣ ከምርምር ተቋማትና ከአጋር ድርጅቶች ጋር የሚያደርገውን ግንኘነት አጠናክሮ እንዲቀጥል አስተያየት ሰጥተዋል፡ከተደረገላቸው ገለጻና በአካል ከተመለከቷቸው የሥራ እንቅስቃሴዎች በመነሳት “ኮርፖሬሽኑ ከተሰጠው ተልዕኮ አንጻር የሚገባውን ያህል ትኩረት አላገኘም” ያሉት የቋሚ ኮሚቴው አባላት በበኩላቸው፣ ኮርፖሬሽኑ የኢትዮጵያን አርሶ አደር አቅፎ የያዘ ተቋም መሆኑን ተረድተናል ብለዋል፡፡አያይዘውም የተቋሙ ስትራተጂክ ዕቅድ ከሀገሪቷ የ10 ዓመት የግብርና ዘርፍ መሪ ዕቅድ ጋር ተጣጥሞ መዘጋጀቱ ለቀጣይ ስኬት ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለተግባራዊነቱም ተገቢውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡
የደን ውጤቶችን (ሙጫ፣ እጣን፣ ከርቤና አበክድ) ለመሰብሰብና ወደ ውጭ ለመላክ የሚደረገው እንቅስቃሴ መጠናከር እንዳለበት፤ የግብርና ግብዓት አቅርቦትን ማስፋት እንደሚገባ፤ የማዳበሪያ ፋብሪካ በሀገር ውስጥ ማቋቋም እንደሚያስፈልግ፤ ለኦርጋኒክ ማዳበሪያ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት እንዲሁም የእርሻና የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች የቴክኒክ ማሠልጠኛ ማዕከልን በአዳዲስ የሥልጠና ማቴሪያሎች ማጠናከር እንደሚገባ የጠቆሙት የቋሚ ኮሚቴው አባላት፣ ኮርፖሬሽኑ ግብርናን ለማዘመን ያከናወናቸውን ሥራዎች በማድነቅ የተቋሙን የሥራ ኃላፊዎች አበረታተዋል፡፡የኮርፖሬሽኑን አጠቃላይ ገጽታ እና የልማት ሥራዎች ለቋሚ ኮሚቴው ገለጻ ያደረጉት የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም፣ በተለይም ከካፒታል ማሳደግ፣ ከአፈር ማዳበሪያ ግዥ ሥርዓት ደንብ ማውጣት፣ ለማዳበሪያ ግዥ የሚሆን ተዘዋዋሪ ፈንድ/Revolving fund ፈቃድ ከማግኘት እንዲሁም ከታክስ ጋር በተያያዘ ያጋጠሙ ችግሮችን ለመቅረፍ እንዲቻል የቋሚ ኮሚቴውን ድጋፍ ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባዘጋጀው የውይይትና የጉብኝት መርሐ ግብር ላይ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ፣ ምክትል ሰብሳቢ፣ ሦስት የንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢዎች፣ 19 አባላት እና ሰባት የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ባለሞያዎች ተገኝተዋል፡፡
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው፡፡