የቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቡሹራ መሐመድ እንዳስታወቁት፣ ጽ/ቤቱ በ2014/15 የምርት ዘመን በባሌ እና አርሲ ዞኖች ከባለሀብቶች እና የግብርና ኮሌጆች በኮንትራት ማዕቀፍ 120 ሺህ ኩንታል ዘር ለማምረት አቅዶ፣ ከ117 ሺህ ኩንታል በላይ ማግኘት ተችሏል ብለዋል፡፡

ይህም የእቅዱን 97.5 ከመቶ ነው ያሉት አቶ ቡሹራ፣ የተሰበሰበው ምርት በጽ/ቤቱ ታሪክ ከፍተኛው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ከተሰበሰበው ዘር ውስጥም ከ10 በላይ የስንዴ እና ገብስ ዝርያዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የተሰበሰበውን ዘር ኮፈሌ ከተማ በሚገኘው የማበጠሪያ ማሽን በማበጠርና በማዘጋጀት ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት ሥራ አስኪያጁ፣ እስከ መጋቢት 12 ቀን 2015 ዓ.ም ድረስ ከ50 ሺህ ኩንታል በላይ ዘር አበጥረው ማዘጋጀታቸውን እና ቀሪው በአጭር ጊዜ ተዘጋጅቶ ለአርሶ አደሩ እንደሚሰራጭ አብራርተዋል፡፡  አቶ ቡሹራ በቀጣይም የምርጥ ዘር አቅርቦትን ለማሳደግ ሌሎች ተጨማሪ ባለሀብቶች ከኮርፖሬሽኑ ጋር በጋራ ዘር እንዲያባዙ  ለማድረግ ማነጋገራቸውንና ከባለሀብቶቹም አዎንታዊ ምላሽ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡ የኮፈሌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በ2014/15 የምርት ዘመን ከኮርፖሬሽኑ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች መካከል በምርጥ ዘር ብዜት ከፍተኛ ምርት በመሰብሰብ ቀዳሚ ሲሆን፣ በቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች ደረጃ 117 ሺህ ኩንታል ምርት ሲሰበሰብ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። በአጠቃላይ በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ደረጃ እስከ አሁን ከተሰበሰበው ከ265 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ውስጥ 105 ሺህ 173 ኩንታል ተበጥሮ ተዘጋጅቷል።

                         ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!