አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 15/2015 ዓ.ም. (ኢግሥኮ):- በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ስር ከሚተዳደሩት እርሻዎች አንዱ በሆነው የአርዳይታ ምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት ከ85 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገለጸ፡፡
የአርዳይታ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ከበደ እንደገለጹት፣ በ2014/15 የመኸር ወቅት 3 ሺህ 70 ሄክታር መሬት በቅድመ መስራች፣መስራች እና የተመሰከረለት ዘር ደረጃዎች መሸፈን ተችሏል፡፡
ከዚህ ውስጥ 2 ሺህ 360 ሄክታር በስንዴ፣ 612 ሄክታር በጎመን ዘር፣ 67 ሄክታር በገብስ እና 31 ሄክታር በባቄላ ዝርያዎች መሸፈኑን አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት አብዛኛው ሰብል በእሸት እና አበባ ደረጃ ይገኛል ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ የሰብሎቹ ሁኔታ በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ የተለየ ተፈጥሮአዊ ችግር ካላጋጠመ በስተቀር ያቀዱትን ከ85 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚያሳኩ አስታውቀዋል፡፡
የአርዳይታ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በቅድመ መስራች፣ መስራች እና የተመሰከረለት የዘር ደረጃ 33 የስንዴ፣ ዘጠኝ የገብስ፣ አንድ የባቄላ እና አንድ የጎመን ዘር ዝርያዎችን እያባዛ ይገኛል፡፡
በሌላ በኩል ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር ለአካባቢው ነዋሪዎች የተለያዩ ድጋፎችን እና ትብብሮችን እያደረገ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ፍቃዱ፣ ለአካባቢው አርሶ አደሮች ዘር ከመሸጫ ዋጋ አምስት በመቶ ቅናሽ በማድረግ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በየዓመቱ በአረም እና ምርት መሰብሰቢያ ወቅት ከ800 እስከ 1000 ለሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች የሥራ እድል እንደሚፈጠርም አስረድተዋል፡፡
ተረፈ ምርትን ወይም የሰብል ገለባን በማኅበር ለተደራጁ የአጎራባች ቀበሌ ሥራ አጥ ወጣቶች በመስጠት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ያለውን ድጋፍም አመልክተዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር በቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ክሊኒክ ለአካባቢው ነዋሪዎች በቅናሽ ዋጋ የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና እርዳታ፣ ነጻ የማዋለድ እና የአምቡላንስ አገልግሎት ድጋፍ እየተሰጠ መሆኑንም አክለው አስታውቀዋል፡፡
የአርዳይታ ምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት ኮርፖሬሽኑ በስሩ ካሉት እርሻዎች መካከል በስፋት ትልቁ ሲሆን፣ መገኛውም በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ገደብ አሳሳ ወረዳ ነው፡፡
### ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!