* በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 46 የአውሮፓ ስሪት ትራክተሮችን ለተጠቃሚዎች አቅርቧል
የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በ2015 በጀት ዓመት 181 ትራክተሮችን ከነመለዋወጫቸው እና ተቀጥላቸው ከውጭ ገበያ በማስመጣት ለተጠቃሚዎች ሊያቀርብ ነው፡፡
በኮርፖሬሽኑ የእርሻ መሣሪያዎች እና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ መንግስቱ ክፍሌ እንደገለጹት፣ ለአማራ ክልል 75 እንዲሁም ለአርሶ አደሮች እና በሰፋፊ እርሻ ለተሰማሩ ባለሃብቶች 106 በድምሩ 181 ዘመናዊ እና አስተማማኝ ትራክተሮችን ለማቅረብ ዝግጅት ተጀምሯል፡፡
የእርሻ መሣሪያዎች የግብርናን ሥራ በማዘመን ምርትና ምርትማነትን በከፍተኛ ደረጃ ይጨምራሉ ያሉት አቶ መንግስቱ፣ ኮርፖሬሽኑ በ2014 በጀት ዓመት በ179 ሚሊዮን ብር ወጪ ከ110 እስከ 180 የፈረስ ጉልበት ያላቸው 46 ትራክተሮችን ከነተቀጥላቸው ከጣሊያን ሀገር በማስመጣት ለተጠቃሚዎች ማቅረቡንም ተናግረዋል፡፡
በአጠቃላይ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ221 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የእርሻ መሣሪያዎች፣ ተቀጥላዎች (ማረሻ፣ መከስከሻ፣ መስመር ማውጫ፣ ዘር መዝሪያ) እና የትራክተር ጋሪዎች ለተጠቃሚዎች መቅረባቸውን ነው ሥራ አስፈጻሚው የገለጹት፡፡
በተጨማሪም 108 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ዋጋ ያላቸው የእርሻ መሣሪያዎች፣ የኮንስትራክሽን ማሽነሪዎች እና የከባድ ተሽከርካሪዎች ጎማ፣ ባትሪ፣ ፊልተር እና ሌሎች መለዋወጫዎችንም አቅርበናል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት የመሬት እና የማሳ ዝግጅት እንዲሁም የምርት መሰብሰብ ሥራዎች ለተጠቃሚዎች ተደራሽ መደረጋቸውን አቶ መንግስቱ አስታውቀዋል፡፡
ከምርት መሰብሰብና ማጓጓዝ አኳያም ሲገልጹ፣ “በዋናነት ለአርሶ አደሮች 192 ሺህ ኩንታል ምርት አጭደን፣ ወቅተን እና አጓጉዘን እስከ ማከማቻ በማድረስ የምርት ብክነት እንዲቀንስ፣ የአርሶ አደሩ ምርታማነት እንዲጨምር እንዲሁም ጊዜውና ጉልበቱ እንዲቆጠብ አድርገናል” ብለዋል፡፡
በመሬት ዝግጅት ረገድም በኦሞ ኩራዝና ጣና በለስ የስኳር ልማት ፕሮጀክቶች ለሸንኮራ አገዳ ልማት እና ለኮርፖሬሽኑ የምርጥ ዘር ማባዣ የሚውል 1 ሺህ 200 ሄክታር መሬት ለእርሻ ምቹ ተደርጎ በኮርፖሬሽኑ መዘጋጀቱንም ተናግረዋል፡፡
በማሣ ዝግጅትም 5 ሺህ 862 ሄክታር መሬት በማረስ፣ በመከስከስ እና ዘር በመዝራት ለተጠቃሚዎች አገልግሎት መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡
በ2015 በጀት ዓመት በ15 የምርት መሰብሰቢያ ኮምባይነሮች እና በ10 የደረቅ ጭነት ማጓጓዣ ተሽከርካሪዎች በመታገዝ የተሻለ የሜካናይዜሽን አገልግሎት ለመስጠት በዝግጅት ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት አቶ መንግስቱ፣ ስለ ትራክተር አያያዝ እና አጠቃቀም በስፋት ሥልጠና ለመስጠት መዘጋጀታቸውንም አያይዘው ጠቁመዋል፡፡
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!