የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢግሥኮ) ከ151 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 46 ዱዝ-ፋር (DEUTZ-FAHR) ትራክተሮችንከጣሊያንሀገርበማስመጣትለተጠቃሚዎችበሽያጭ አስረክቧል፡፡ ከ110 እስከ 180 የፈረስ ጉልበት ያላቸው እነዚህ ትራክተሮች በሽያጭ የቀረቡት ለአማራ ክልል ግብርና ቢሮ፣ ለሲዳማ ክልል እርሻ እና የተፈጥሮ ሃብት ቢሮ እንዲሁም ለእንጅባራ፣ ደብረ ብርሃን እና ጎንደር ዩኒቨርሲቲዎች፤ ለአጋርፋ ግብርና ኮሌጅ እና በእርሻ ሥራ ላይ ለተሰማሩ ባለሃብቶች ነው፡፡ ትራክተሮቹ የ2021 እና 2022 ምርት በመሆናቸው ዘመኑ የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ከማሟላታቸው ባሻገር ለሀገራችን የአየር ንብረትና የመሬት አቀማመጥ ተስማሚ ስለመሆናቸው ተጠቃሚዎች ይመሰክራሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ትራክተሮቹ በሀገራችን ሜካናይዝድ እርሻን ለማስፋፋት፣ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እና የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖራቸው ይታመናል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ኮርፖሬሽኑ የተጨማሪ 12 ዱዝ-ፋር ትራክተሮች ግዥ የፈጸመ ሲሆን፣ ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ሀገር ውስጥ ይደርሳሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በቀጣይም የአመራረት ዘዴን በቴክኖሎጂ የተደገፈ ለማድረግ ዘመናዊ፣ አስተማማኝና ጥራት ያላቸውን የእርሻ መሣሪያዎች እስከ መለዋወጫቸው ከውጭ ሀገር በማስመጣት ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው፡፡ በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ ለሚያቀርባቸው ትራክተሮች ከሽያጭ በኋላ የጥገና፣ የቴክኒክ ሞያ ሥልጠና እንዲሁም መለዋወጫዎችን የማቅረብ አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡ እንዲሁም ከግብርና ማሳደጊያዎች ግብዓት እና መሣሪያዎች አቅርቦት በተጨማሪ ከመሬት ዝግጅት እስከ ጎተራ የሚዘልቅ የተቀናጀ የግብርና ሜካናይዜሽን አገልግሎት ተደራሽ እያደረገ ይገኛል፡፡ በተጨማሪ የእርሻና የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች ኪራይ፣ የደረቅ ጭነት ትራንስፖርት፣ የተሽከርካሪዎች ጥገና፣ የዘር ብጠራ እና የማማከር ሥራ በኮርፖሬሽኑ የሚሰጡ ሌሎች አገልግሎቶች ናቸው፡፡ በአምስት ትላልቅ የልማት ደርጅቶች ውህደት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 368/2008 መሠረት ታህሳስ 2008 ዓ.ም የተቋቋመው የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን (ኢግሥኮ) ለግብርና ምርትና ምርታማነት እድገት እና ለዘርፉ መዘመን የላቀ አስተዋጽዖ ያላቸውን ምርጥ ዘር፣ የአፈር ማዳበሪያ፣ አግሮኬሚካልና የኬሚካል መርጫ መሣሪያዎችን እንዲሁም የእርሻ መሣሪያዎችን ከነመለዋወጫቸው ለተጠቃሚዎች በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ ላይ ይገኛል።
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!