ነሐሴ 4/2013 (ኢዜአ) የደን ውጤት የሆኑ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ ከ900 ሺህ ዶላር በላይ መገኘቱን የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ገለፀ።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም የተቋሙን የ2013 በጀት ዓመት ስራ አፈፃፀም አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው የምርጥ ዘር፣ የደን ውጤቶችና የግብርና ምርት ማሳደጊያ አቅርቦቶችን ጨምሮ የእርሻ መሳሪያዎች አቅርቦትና የሜካናይዜሽን አገልግሎትን ከማስፋት አኳያ የተሰሩ ስራዎችን አብራርተዋል።
የደን ውጤቶች የሆኑትን እንደ ሙጫ፣ እጣን፣ ከርቤ እና አበክድ ምርቶችን ወደ ውጭ በመላክ በበጀት ዓመቱ ከ900 ሺህ በላይ ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅሰዋል።
ገቢው የተገኘው የደን ውጤቶችን ለማምረት በማኅበር ከተደራጁ ወጣቶች ከተሰባሰበው ከሁለት ሺህ ኩንታል በላይ ምርት እንደሆነም ገልጸዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው በበጀት ዓመቱ ከ13 ሺህ ሄክታር በሚልቅ መሬት ከ284 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ማምረት እንደተቻለ ገልጸዋል።
በበጀት ዓመቱ ከ172 ሺህ 395 ኩንታል ምርጥ ዘር ከ617 ሚሊዮን ብር በላይ ሽያጭ መከናወኑን አክለዋል።
በሌላ በኩል በግብርና ምርት ማሳደጊያ አቅርቦት ከ600 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ከውጭ አገር የአፈር ማዳበሪያ፣ ፀረ አረም እና ተባይ ኬሚካሎች ተገዝተው ለተጠቃሚዎች መሰራጨታቸውን ተናግረዋል።
የዓለም ገበያ የማዳበሪያ ዋጋ ጭማሪ አርሶ አደሩን እንዳይጫን ኮርፕሬሽኑ ከ60 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ በመውሰድና መንግሥት በበኩሉ ከ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በላይ የትራንስፖርት ወጪ በመሸፈን ተሰራጭቷል ብለዋል።
የእርሻ መሳሪያዎች አቅርቦትና የሜካናይዜሽን አገልግሎትን ከማስፋት አንፃርም ከ73 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው የእርሻ መሳሪያዎችና መለዋወጫዎች ለተጠቃሚዎች ቀርበዋል ብለዋል።
አቶ ክፍሌ አያይዘውም በ2014 በጀት ዓመት ምርጥ ዘር የማባዛትና የማሰራጨት ስራ በትኩረት እንደሚከናወን ጠቁመዋል።
በአገሪቷ ሁሉም አከባቢዎች የሚገኙ የኮርፖሬሽኑ መሬቶች ፆም እንዳያድሩ እየተሰራ መሆኑንም አክለዋል።
የግብርና ግብዓቶች አቅርቦትን ለማሳደግና ተደራሽ ለማድረግ፣ የተቀናጀ የሜካናይዜሽን አገልግሎት ለማስፋትና ከክልሎች የተገኙ የእርሻ መሬቶችን ለማልማት እንቅስቃሴ መጀመሩንም ነው የተናገሩት። የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የግብርና ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶና አርብቶ አደሩ ተደራሽ በማድረግ የአገሪቷን የምጣኔ ሀብት እድገት የማገዝ ዓላማ አንግቦ የሚሰራ ተቋም ነው