“ኮርፖሬሽኑ ካለው አፈጻጸምና ልምድ አንጻር በ2014 በጀት ዓመት የተሻለ ውጤት እንደሚያስመዘግብ ተስፋ አደርጋለሁ” የኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ
የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽንን ወደ ተሻለ የእድገት ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ አዳዲስ ሃሳቦችን ማፍለቅ እንደሚገባ የኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ ገለጹ፡፡
የቦርድ ሰብሳቢው ዶክተር ግርማ አመንቴ ይህንን የገለጹት ነሐሴ 22/2013 ዓ.ም በተካሄደ የኮርፖሬሽኑ የሠራተኞች አመታዊ ስብሰባ ላይ ነው፡፡
በስብሰባው ወቅት የተቋሙ የ2013 በጀት ዓመት አፈጻጸምና የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ ቀርቦ ውይይቱን የቦርድ ሰብሳቢው መርተውታል፡፡
በ2013 በጀት ዓመት የተገኘውን አበረታች ውጤት ያደነቁት ሰብሳቢው፣ እያንዳንዱ ሠራተኛ እኔ ሰርቼ ያመጣሁት ውጤት ነው የሚል አስተሳሰብ ማዳበር እንዳለበት አስረድተዋል፡፡
ይሁንና በአንዱ ትክሻ ሌላው ቁጭ ብሎ ሳይሰራ መጠቀም እንደሌለበትም አስገንዝበዋል፡፡ ከሥራ ክፍል አኳያም አንዱ ያተረፈውን ሌላው እየበላ ኮርፖሬሽኑን ለኪሳራ መዳረግ እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ ባለው የእርሻ መሬት ሁለቴና ሦስቴ ማምረት እንደሚጠበቅበት የገለጹት ዶክተር ግርማ፣ ከዚህ ባሻገር ከክልሎች ጋር በቅርበት በመነጋገርና በመስራት ተጨማሪ አዳዲስ የእርሻ መሬቶችን ማፈላለግና ማልማት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡
የኮርፖሬሽኑን የ2014 በጀት ዓመት ዕቅድ አስመልክተው ሲናገሩም ድርጅቱ ካለው አፈጻጸምና ልምድ አንጻር በበጀት ዓመቱ የተሻለ ውጤት እንደሚያስመዘግብ ተስፋ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡ ለዕቅዱ ስኬትም እንደምንግዜውም ሁሉ የቦርዱ ድጋፍና ክትትል እንደማይለይ በራሳቸውና በሥራ አመራር ቦርዱ ስም አረጋግጠዋል፡፡
የእለቱን ስብሰባ በንግግር የከፈቱት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደማርያም በበኩላቸው፣ ኮርፖሬሽኑ ከተቋቋመበት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በማኔጅመንቱና በሠራተኛው ከፍተኛ ጥረት እንዲሁም በተቋሙ የሥራ አመራር ቦርድ እና በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ ሁለገብ ድጋፍ በየአመቱ ትርፋማነቱን አስጠብቆ መዝለቁን ተናግረዋል፡፡
“በተለይም በ2013 በጀት ዓመት በኮሮና ቫይረስ በሽታ ወረርሽኝ፣ በጸጥታ ችግሮችና በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ ባጋጠመን ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ሆነን የተገኘ ትርፍ አፈጻጸም ካለፉት አራት ዓመታት አማካይ እና ከ2012 በጀት አመት አፈጻጸም ጋር ሲነጻጸር በቅደም ተከተል 42% እና 8% እድገት አሳይቷል” ብለዋል፡፡
ለውጤቱ መሳካትም የበኩላቸውን ድጋፍ ላደረጉ የኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ እና በገንዘብ ሚኒስቴር የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ክትትልና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት ምስጋና አቅርበዋል፡፡
በተመሳሳይ የተቋሙ የመሰረታዊ የሠራተኛ ማኅበር፣ መላው የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ለኮርፖሬሽኑ ዕቅድ መሳካት ላበረከቱት አስተዋጽዖ በኮርፖሬሽኑ እና በራሳቸው ስም አመስግነዋል፡፡ በስብሰባው ላይ የሥራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ እና የገንዘብ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡