ኮርፖሬሽኑ በስንዴ ልማት ለአበረከተው የላቀ አስተዋጽዖ እውቅና አገኘ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም (ኢግሥኮ):- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በሀገር አቀፍ ደረጃ በስንዴ ልማት ከሀገራዊ ፍላጎት እስከ ውጭ ገበያ አቅራቢነት በመሸጋገር ሂደት ለአበረከተው የላቀ አስተዋጽዖ የምስጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቶታል።
ኮርፖሬሽኑ ይህንን እውቅና ያገኘው “የመሻገር ጥሪቶች፣ የአዲስ ብርሃን ወረቶች” በሚል መሪ ሀሳብ ጳጉሜን 1 ቀን 2016 ዓ.ም ‘የመሻገር ቀን’ በሳይንስ ሙዚየም በተከበረበት ወቅት ነው፡፡
የኮርፖሬሽኑ የኦፕሬሽን ዐቢይ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፈለቀ ገዛኸኝ ለተቋሙ የተበረከተውን ሽልማት ከኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እጅ ተቀብለዋል።በተመሳሳይ ኮርፖሬሽኑ የ2016/17 ምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ ግዥ፣ አቅርቦት እና ሥርጭት እንዲሳለጥ ለአበረከተው የጎላ አስተዋጽዖ ነሐሴ 29 ቀን 2016 ዓ.ም ከግብርና ሚኒስቴር የእውቅናና የምስጋና የምስክር ወረቀት እና ዋንጫ ማግኘቱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ለግብርና መዘመንና ለምርታማነት እድገት የላቀ አስተዋጽዖ ያላቸውን ምርጥ ዘር፣ ጠጣርና ፈሳሽ የአፈር ማዳበሪያ፣ አግሮኬሚካሎች እና የእንስሳት መድኃኒቶችን ለተጠቃሚዎች በማቅረብ ይታወቃል፡፡
በተጨማሪም የእርሻ፣ የኮንስትራክሽን እና የኬሚካል መርጫ መሣሪያዎችና መለዋወጫዎችን በማቅረብ፤ ከሽያጭ በኋላ የጥገና፣ የምክር፣ የቴክኒክና ሞያ ሥልጠና አገልግሎቶችን በመስጠት እንዲሁም የዘር ብጠራ እና የደረቅ ጭነት ትራንስፖርት አገልግሎቶችን ተደራሽ በማድረግ የተሰጠውን ተልእኮ እየተወጣ ይገኛል።
በሌላ በኩል እጣን፣ ሙጫ፣ ከርቤና አበከድ ለውጭ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ የሚገኝ የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው፡፡
###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!