አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢግሥኮ):-  የ2019 አዲስ ዓመትን እና የኅብር ቀንን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለተቋሙ የቀን ሠራተኞች ጳጉሜን 4 ቀን 2018 ዓ.ም ማዕድ አጋሩ።

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ሮ የሺእመቤት ነጋሽ ከተቋሙ የበላይ አመራሮች ጋር በመሆን በኮርፖሬሽኑ ዋና መ/ቤትና በአዳማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ለሚያገለግሉ 140 የቀን ሠራተኞች ማዕድ አጋርተዋል።

በዕለቱ በ805 ሺህ ብር ወጪ የተገዙ ዱቄት፣ ዘይት፣ ዶሮና እንቁላል ድጋፍ ተደርጓል።

ድጋፍ የተደረገላቸው፣ ወደ ውጭ ገበያ  የእጣንና የሙጫ ምርት ዝግጅት ላይ በቀን ሥራ ላይ የተሰማሩ 45 ሴቶች እና በዋና መ/ቤት በፅዳት፣ በጉልበት ሥራና በካፍቴሪያ የሚያገለግሉ 95 የቀን ሠራተኞች ናቸው።

በዕለቱ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ የሺእመቤት ነጋሽ ባስተላለፉት መልእክት፣ መርሐ ግብሩ ኮርፖሬሽኑ ከቀን ሠራተኞች ጋር ያለውን አብሮነትና አጋርነት የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸው፣ ወደፊትም አቅም በፈቀደ መጠን  አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አስታውቀዋል።

ድጋፍ የተደረገላቸው ሠራተኞች በበኩላቸው፣ “እንደ ሠራተኛ ተቆጥረን፣ አስታዋሽ በማግኘታችን ደስተኞች ነን።” በማለት፣ ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

በኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሀሳብ አመንጪነት በተቋሙ የተጀመረው ማዕድ ማጋራት፣ የዓለም የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ከ600 ሺህ ብር በላይ ወጪ ለ126 የኮርፖሬሽኑ የቀን ሠራተኞች ድጋፍ መደረጉ ይታወሳል።
                 ###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!