አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፦ የሩሲያ ስሪት የሆኑ የእርሻ መሣሪያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ለኢትዮጵያ አርሶ አደሮችና ሌሎች ተጠቃሚዎች ማቅረብ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ነሐሴ 28 ቀን 2018 ዓ.ም ውይይት ተደረገ።
ውይይቱ የተደረገው በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የበላይ አመራሮችና በሩሲያ የልዑካን ቡድን መካከል ነው።
በኮርፖሬሽኑ ዋና መ/ቤት በተካሄደው በዚህ ውይይት፣ ኮርፖሬሽኑ የእርሻ መሣሪያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ከሩሲያ ለማስመጣት ፍላጎት እንዳለው ተገልጿል።
በዚሁ ወቅት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ የሺእመቤት ነጋሽ፣ የሜካናይዜሽን አገልግሎትን ማስፋፋትና ግብርናን ማዘመን የመንግሥት ቀዳሚ አጀንዳና ትኩረት መሆኑን አስታውቀው፣ ከዚህ የተነሳ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የእርሻ መሣሪያዎች ፍላጎት መኖሩን አብራርተዋል።
የሩሲያ የግብርና ማሽነሪ አምራቾች በበኩላቸው የሚያመርቷቸውን የእርሻ መሣሪያዎችና ቴክኖሎጂዎች በተመለከተ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፣ ኮርፖሬሽኑም የሚፈልጋቸውን የማሽነሪ አይነቶችና ፍላጎቶች ለልዑካን ቡድኑ አቅርቧል።
በቀጣይ አጋርነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ተጨማሪ ውይይቶችንና የመስክ ጉብኝቶችን ለማድረግ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።
ሩሲያ እና ኢትዮጵያ የረጅም ዓመታት ወዳጅነት፣ ትብብርና አጋርነት ያላቸው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የአፈር ማዳበሪያ ከሚያስመጣባቸው ሀገራት አንዷ ሩሲያ ናት።
###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!









