የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን Ethiopian Agricultural Businesses Corporation

ኮርፖሬሽኑ ከቻይና ኩባንያ ጋር ለመሥራት ተወያየ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 19 ቀን 2019 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፦ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አመራሮች ከቻይና መንግሥታዊ የግብርና መሣሪያዎች አምራችና አቅራቢ ድርጅት – ‘ሎቮል’ – Lovol የሥራ ኃላፊዎች ጋር በሁለትዮሽ ትብብር አብሮ መሥራት በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መስከረም 19 ቀን 2019 ዓ.ም በተቋሙ ዋና መ/ቤት ተወያዩ።

‘ሎቮል’ – Lovol ተብሎ የሚታወቀው ኩባንያ በቻይና ቀዳሚ የእርሻ መሣሪያዎች አምራች እንደሆነ እና ከ120 በላይ የዓለም ሀገራት ምርቶቹን እንደሚያቀርብ በውይይቱ ተጠቁሟል።

በወቅቱ የ’ሎቮል’ ስሪት የሆኑ ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎችን እና ቴክኖሎጂዎችን በኮርፖሬሽኑ በኩል ለአርሶ አደሩና ለተለያዩ ተጠቃሚዎች ተደራሽ ማድረግ በሚቻልባቸው እድሎች ዙሪያ ውይይት ተደርጓል።

በዕለቱ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወካይና ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደሳለኝ በላቸው እና ሌሎች የተቋሙ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም በ’ሎቮል’ በኩል የኩባንያው የአፍሪካና የኢትዮጵያ ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
               ###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!

ኮርፖሬሽኑ ለአቅመ ደካሞች ማዕድ አጋራ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 1 ቀን 2019 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፦ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የ2019 ዘመን መለወጫን ምክንያት በማድረግ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 በሚገኘው የተስፋ ብርሃን ምገባ ማዕከል ለአቅመ ደካሞች ማዕድ አጋራ።

መስከረም 1 ቀን በተካሄደው የማዕድ ማጋራት መርሐ ግብር ላይ የተገኙት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ የሺእመቤት ነጋሽ፣ ተቋሙ የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከሚያደርገው ዘርፈ ብዙ ጥረት ጎን ለጎን ለማኅበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከዚህ አኳያ ኮርፖሬሽኑ ለሀገር ውለታ የዋሉ አረጋውያንን፣ አቅመ ደካሞችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ ሴቶችንና ሕፃናትን እንዲሁም አስታዋሽ የሌላቸውን ዜጎች ለመደገፍ፣ ከጎናቸው ለመቆምና በዓሉን በደስታ እንዲያሳልፉ ለማድረግ ማዕድ ማጋራቱን አስታውቀዋል።

በዕለቱ በተዘጋጀው መርሐ ግብር ላይ የኮርፖሬሽኑ የበላይ አመራሮች፣ የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ም/ዋና ሥራ አስፈጻሚና የሥራና ክህሎት ጽ/ቤት ኃላፊ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር እንዲሁም  የክፍለ ከተማው እና የወረዳ 1 አስተዳደር አመራሮች ተገኝተዋል።

ኮርፖሬሽኑ ሰሞኑን በዋና መ/ቤት በፅዳት፣ በጉልበት ሥራና በካፍቴሪያ ለሚያገለግሉ እንዲሁም በአዳማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የውጭ ምንዛሬ በሚያስገኘው የእጣንና የሙጫ ምርት ዝግጅት ላይ በቀን ሥራ ለተሰማሩ በአጠቃላይ ለ140 የቀን ሠራተኞች የአዲስ ዓመት በዓል መዋያ ማዕድ ማጋራቱ ይታወሳል።
                  ###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለቀን ሠራተኞች ማዕድ አጋሩ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢግሥኮ):-  የ2019 አዲስ ዓመትን እና የኅብር ቀንን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ለተቋሙ የቀን ሠራተኞች ጳጉሜን 4 ቀን 2018 ዓ.ም ማዕድ አጋሩ።

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ሮ የሺእመቤት ነጋሽ ከተቋሙ የበላይ አመራሮች ጋር በመሆን በኮርፖሬሽኑ ዋና መ/ቤትና በአዳማ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ለሚያገለግሉ 140 የቀን ሠራተኞች ማዕድ አጋርተዋል።

በዕለቱ በ805 ሺህ ብር ወጪ የተገዙ ዱቄት፣ ዘይት፣ ዶሮና እንቁላል ድጋፍ ተደርጓል።

ድጋፍ የተደረገላቸው፣ ወደ ውጭ ገበያ  የእጣንና የሙጫ ምርት ዝግጅት ላይ በቀን ሥራ ላይ የተሰማሩ 45 ሴቶች እና በዋና መ/ቤት በፅዳት፣ በጉልበት ሥራና በካፍቴሪያ የሚያገለግሉ 95 የቀን ሠራተኞች ናቸው።

በዕለቱ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ የሺእመቤት ነጋሽ ባስተላለፉት መልእክት፣ መርሐ ግብሩ ኮርፖሬሽኑ ከቀን ሠራተኞች ጋር ያለውን አብሮነትና አጋርነት የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸው፣ ወደፊትም አቅም በፈቀደ መጠን  አስፈላጊው ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አስታውቀዋል።

ድጋፍ የተደረገላቸው ሠራተኞች በበኩላቸው፣ “እንደ ሠራተኛ ተቆጥረን፣ አስታዋሽ በማግኘታችን ደስተኞች ነን።” በማለት፣ ለተደረገላቸው ድጋፍ አመስግነዋል።

በኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሀሳብ አመንጪነት በተቋሙ የተጀመረው ማዕድ ማጋራት፣ የዓለም የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ከ600 ሺህ ብር በላይ ወጪ ለ126 የኮርፖሬሽኑ የቀን ሠራተኞች ድጋፍ መደረጉ ይታወሳል።
                 ###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!

የሩሲያ የእርሻ መሣሪያዎችን ለአርሶ አደሮች ማቅረብ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ውይይት ተደረገ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 28 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፦ የሩሲያ ስሪት የሆኑ የእርሻ መሣሪያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ለኢትዮጵያ አርሶ አደሮችና ሌሎች ተጠቃሚዎች ማቅረብ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ነሐሴ 28 ቀን 2018 ዓ.ም  ውይይት ተደረገ።

ውይይቱ የተደረገው በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የበላይ አመራሮችና በሩሲያ የልዑካን ቡድን መካከል ነው።

በኮርፖሬሽኑ ዋና መ/ቤት በተካሄደው በዚህ ውይይት፣ ኮርፖሬሽኑ የእርሻ መሣሪያዎችንና ቴክኖሎጂዎችን ከሩሲያ ለማስመጣት ፍላጎት እንዳለው ተገልጿል።

በዚሁ ወቅት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ የሺእመቤት ነጋሽ፣  የሜካናይዜሽን አገልግሎትን ማስፋፋትና ግብርናን ማዘመን የመንግሥት ቀዳሚ አጀንዳና ትኩረት መሆኑን አስታውቀው፣ ከዚህ የተነሳ በኢትዮጵያ ከፍተኛ የእርሻ መሣሪያዎች ፍላጎት መኖሩን አብራርተዋል።

​የሩሲያ የግብርና ማሽነሪ አምራቾች በበኩላቸው የሚያመርቷቸውን የእርሻ መሣሪያዎችና ቴክኖሎጂዎች በተመለከተ ገለጻ ያደረጉ ሲሆን፣ ኮርፖሬሽኑም የሚፈልጋቸውን የማሽነሪ አይነቶችና ፍላጎቶች ለልዑካን ቡድኑ አቅርቧል።

በቀጣይ አጋርነትን ለማጠናከር የሚያስችሉ ተጨማሪ ውይይቶችንና የመስክ ጉብኝቶችን ለማድረግ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።

ሩሲያ እና ኢትዮጵያ የረጅም ዓመታት ወዳጅነት፣ ትብብርና አጋርነት ያላቸው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የአፈር ማዳበሪያ ከሚያስመጣባቸው ሀገራት አንዷ ሩሲያ ናት።
                ###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!