አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢግሥኮ):- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዓመታዊ በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ነሐሴ 23 ቀን 2018 ዓ.ም በኮርፖሬሽኑ ዋና መስሪያ ቤት ተከበረ።

በዚህ ወቅት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ የሺእመቤት ነጋሽ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግር፣ የ2018 በጀት ዓመት ኮርፖሬሽኑን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሸጋግሩ መሠረቶች የተጣሉበት ዓመት መሆኑን ገልጸዋል። በተለይም በተቋሙ አሠራር፣ አደረጃጀት፣ በንብረት አስተዳደርና አያያዝ አዎንታዊ ለውጦች መደረጋቸውን አብራርተዋል።

በበጀት ዓመቱ በገቢና በትርፍ በኩል ከዕቅድ በላይ አፈጻጸም መመዝገቡን የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፣ አፈጻጸሙ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከተመዘገበው አፈጻጸም የላቀ መሆኑን አስታውቀዋል።

ለዚህ ስኬት መገኘት የኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት፣ የኮርፖሬሽኑ አመራሮችና ሠራተኞች፣ ደንበኞች እንዲሁም የሌሎች ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ርብርብ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱን በመጠቆም ምስጋና አቅርበዋል።

​የሥራ አመራር ቦርድ አባል አቶ ዳንኤል ስለሺ በበኩላቸው፣ ቦርዱ ከኮርፖሬሽኑ አመራርና ሠራተኞች ጎን በመሆን ለአዎንታዊ ለውጦች መመዝገብ የድርሻውን መወጣቱን ገልጸው፣ በቀጣይም አስፈላጊው ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።

የመሠረታዊ ሠራተኞች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ብርሃኑ ደበሌ በበጀት ዓመቱ አመራሩና ሠራተኛው በመተባበር ላስመዘገቡት ውጤት ምስጋና አቅርበው፤ በቀጣይም እያንዳንዱ ሠራተኛ በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በብቃት በመወጣት ለጋራ ስኬት እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።

​በዝግጅቱ ማጠቃለያ ላይ ለተቋሙ ውጤታማነት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም ኮርፖሬሽኑን ለበርካታ ዓመታት አገልግለው በጡረታ ለተሰናበቱ አመራሮችና ሠራተኞች የምስጋና እና የእውቅና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷቸዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተርና የኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ አባል ማንደፍሮ ንጉሤ (ዶ/ር)፣ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መለሰ መና እና የኮሚቴው አባላት እንዲሁም የኢትዮ ኢንጅነሪንግ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኮሌኔል ሸጋው ሙሉጌታ እና ሌሎች የባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።
###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!