አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 21 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፦ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ከፍተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ (ኢኢሆ) ገለጸ።

የኮርፖሬሽኑ አፈጻጸም ነሐሴ 21 ቀን 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በተገመገመበት ወቅት፣ ተቋሙ ያስመዘገበው አፈጻጸም ከፍተኛ መሆኑን የሆልዲንጉ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሀብታሙ ኃይለሚካኤል አስታውቀዋል።

የኮርፖሬሽኑ አዲሱ አመራር በኃላፊነት በመሥራቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ሊያመጣ ችሏል ያሉት አቶ ሀብታሙ፣ የተቋሙን ገጽታ በመጠበቅና ልማቱን በማስቀጠል በኦፕሬሽን፣ በፋይናንስና በማኅበራዊ ኃላፊነት ያስመዘገበውን ከፍተኛ ውጤት ኢኢሆ ያደንቃል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በ2018 በጀት ዓመት ከ438 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ያመረተ ሲሆን፣ ከ20.8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለተጠቃሚዎች አቅርቧል።

በፋይናንስ ረገድም፣ የኮርፖሬሽኑ የ2018 በጀት ዓመት ገቢና ትርፍ ካለፉት ሦስት ዓመታት (ከ2015-2017) ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ የ15.3 ቢሊዮን ብር ገቢና የ3.6 ቢሊየን ብር ትርፍ ተመዝግቧል።
               ###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!