አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 14 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢግሥኮ):- በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የኮፈሌ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በ2018 በጀት ዓመት ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን ዘርና የምግብ እህል ለአርሶ አደሮችና ሌሎች ተጠቃሚዎች መሸጡን ገለጸ።

የጽ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቡሽራ መሐመድ እንደገለጹት፣ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ በበጀት አመቱ ከ1.4 ቢሊየን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን 58 ሺህ 884 ኩንታል ምርጥ ዘርና 49 ሺህ 50 ኩንታል የምግብ እህል ለገበያ አቅርቧል።
በተጨማሪም ቅርንጫፉ በኮፈሌ ከተማ ባለው የዘር ማበጠሪያና ማዘጋጃ ማዕከል 55 ሺህ 737 ኩንታል ዘር አበጥሮ በማዘጋጀት ለአርሶ አደሮች ማቅረቡን ሥራ አስኪያጁ አስታውቀዋል።
በሌላ በኩል በበጀት ዓመቱ በኮንትራት እርሻ በተለይም በባሌ ዞኖች በሚገኙ ሰፋፊ የመንግሥትና የባለሀብት እርሻዎች 6 ሺህ 244 ሄክታር መሬት በዘር በመሸፈን ከ155 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት በትብብር መመረቱን አቶ ቡሽራ ተናግረዋል።
የቅርንጫፉ የዘር አቅርቦት በኮፈሌ፣ ዶዶላ፣ ገደብ አሳሳ፣ ሻሸመኔ፣ አርሲ ነገሌና በባሌ ዞን አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደሮችንና ሌሎች ተጠቃሚዎችን ተደራሽ ያደርጋል።
በ1971 ዓ.ም የተቋቋመው የኮፈሌ ቅርንጫፍ፣ ከኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አንጋፋ ቅርንጫፎች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በዋናነት በምርጥ ዘር ምርት፣ ዝግጅትና አቅርቦት ሥራ ላይ ተሰማርቶ እየሠራ ይገኛል።
###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!


