ሀዋሳ፣ ነሐሴ 4 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፡- በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሀዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት በኮንትራት እርሻ ውል በሰፋፊ የመንግሥትና ባለሀብት እርሻዎች ዘር እያባዛ መሆኑን ገለጸ፡፡

የጽ/ቤቱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፈቃዱ ከበደ እንደገለጹት፣ ቅርንጫፉ በአላጌ ግብርና ቴክኒክና ሞያ ሥልጠና ኮሌጅ እንዲሁም በአላባና ስልጤ ዞኖች በሚገኙ የባለሀብት ሰፋፊ እርሻዎች የስንዴ፣ የበቆሎና የቦለቄ ዘር እያባዛ ይገኛል። እስከ አሁንም 2 ሺህ 140 ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑን ጠቁመዋል።
በተጨማሪ በጉራጌ ዞን አበሽጌ ወረዳ በ300 ሄክታር መሬት ላይ የዘር ብዜት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ያመለከቱት አቶ ፈቃዱ፣ በአሁኑ ወቅት ከኮርፖሬሽኑ ጋር ውል ገብተው ዘር እያባዙ ለሚገኙ አካላት አስፈላጊው የአግሮኖሚ፣ የሞያና የሰብል እንክብካቤ ድጋፍ እንዲሁም የጥራት ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን አስታውቀዋል።
ቅርንጫፉ ከዘር ብዜት ባሻገር በምግብ እህል ምርት ላይ እየሠራ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ፣ በምዕራብ ሸዋ ዞን ወሊሶ አካባቢ ከአንድ ባለሀብት ጋር በመተባበር በ150 ሄክታር መሬት ላይ ለምግብነት የሚውል በቆሎ እያስመረተ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የግብርና ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከራሱ እርሻዎች በተጨማሪ በሰፋፊ የመንግሥትና ባለሀብት እርሻዎች እንዲሁም በክላስተር በተደራጁ አርሶ አደሮች ማሳ ዘር በማባዛት ለተጠቃሚዎች እያቀረበ የሚገኝ የመንግሥት የልማት ድርጅት ነው፡፡
###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!


