- በክልሉ በልማት ማኅበር ለተደራጁ ሴቶች የወተት ላሞችና ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል

አለታ ወንዶ፣ ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢግሥኮ):- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በበጎ አድራጎት የክረምት ሥራዎች በሲዳማ ክልል ደቡባዊ ሲዳማ ዞን አለታ ወንዶ ወረዳ የመዋለ ሕፃናት ት/ቤት ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም አስቀመጠ።
ከዚህ በተጨማሪ ኮርፖሬሽኑ በክልሉ በሴቶች ልማት ቡድን ለተደራጁ እናቶች ዝርያቸው የተሻሻለ ስምንት የወተት ላሞችን የለገሰ ሲሆን፣ ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
የትምህርት ቤት ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጡት የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ የሺእመቤት ነጋሽ፣ ትምህርት ቤቱ በአጭር ጊዜና በጥራት ተገንብቶ ለአገልግሎት እንዲበቃ ኮርፖሬሽኑ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ኮርፖሬሽኑ በአለታ ወንዶ ወረዳ ለሩንጃ ዊቾ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት 250 ተማሪዎች 3000 ደብተር፣ 3000 እስክሪብቶ፣ 3000 እርሳስ እና 250 ቦርሳ ድጋፍ አድርጓል።
በሌላ በኩል ከ700 ሺህ ብር በላይ በሆነ ወጪ በደቡባዊ ሲዳማ ዞን ቡርሳ ወረዳ ለሚገኙ በማኅበር ለተደራጁ እናቶች የተደረገው የወተት ላሞች ድጋፍ የሴቶችን ኑሮ ለማሻሻል አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ተገልጿል።
ወይዘሮ የሺእመቤት በመልእክታቸው ማጠቃለያ፣ ኮርፖሬሽኑ በደቡባዊ ሲዳማ ዞን ሁለት ወረዳዎች ባከናወናቸው የበጎ አድራጎት ሥራዎች አረንጓዴ አሻራ ከማሳረፍ ባሻገር ለትውልድ ግንባታ ትኩረት በመስጠት ት/ቤት ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ ማስቀመጡንና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን እንዲሁም የሌማት ትሩፋት ሥራን መፈጸሙን ተናግረዋል።
በዕለቱ የተገኙት የደቡባዊ ሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መንገሻ ፊታሞ፣ የሲዳማ ክልል የብልጽግና ፓርቲ የዴሞክራሲ ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ፣ የክልሉ የሴቶችና ወጣቶች ማኅበራዊ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ፣ የአለታ ወንዶና የቡርሳ ወረዳዎች የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ኮርፖሬሽኑ ላደረገው በጎ ተግባር አመስግነዋል።
በመጨረሻም ለኮርፖሬሽኑ አመራሮች የደቡባዊ ሲዳማ ዞን አካባቢን ባህል የሚያንጸባርቁ ሥጦታዎች ተበርክቶላቸዋል።
###
ግብርናን እያዘመንን ማኅበራዊ ኃላፊነትን እንወጣለን!




