አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 17 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢግሥኮ):- በኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የጎንዴ ኢተያ ምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት በዘር እየተሸፈነ ነው።

በኮርፖሬሽኑ የአሰላ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሃኑ የሺጥላ እንደገለጹት፣ በጎንዴ ኢተያ እርሻ እስከ አሁን 282 ሄክታር መሬት በስንዴ፣ በገብስ፣ በጎመን ዘርና በበቆሎ ምርጥ ዘር ተሸፍኗል።
ሰብሎቹ በጥሩ የብቅለት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ያስታወቁት አቶ ብርሃኑ፣ በተመሳሳይ የሽንብራና የጤፍ ሰብል ዝርያዎችን በነሐሴ ወር ለመዝራት የሚያስችል አብዛኛው የመሬት ዝግጅት ሥራ መጠናቀቁን ገልጸዋል።
ቅርንጫፍ ጽ/ቤቱ ዘር ከማባዛት በተጨማሪ አሰላ ከተማ ባለው የዘር ማበጠሪያና ማዘጋጃ ማዕከል አማካኝነት ዘር በማበጠርና በማዘጋጀት ለአርሶ አደሮችና ለሌሎች ተጠቃሚዎች እያቀረበ እንደሚገኝ አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል።
ሌላኛው የኮርፖሬሽኑ የአርዳይታ ምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት 3 ሺህ 80 ሄክታር መሬት በ17 አይነት የሰብል ዝርያዎች ሙሉ በሙሉ መሸፈኑን መዘገባችን ይታወሳል።
###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!


