አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፦ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በ2018 በጀት ዓመት የላቀ የዕቅድ አፈጻጸም አስመዘገበ።

የኮርፖሬሽኑ ሥራ አመራርና የመሠረታዊ የሠራተኛ ማኅበር አመራሮች በተገኙበት ሐምሌ 9 ቀን 2018 ዓ.ም በተቋሙ ዋና መ/ቤት በተካሄደ ዓመታዊ የአፈጻጸም ግምገማ ላይ የበጀት ዓመቱ ዕቅድ አፈጻጸም በአሠራር፣ በገቢና ትርፍ ካለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት (ከ2015-2017) የተሻለና ከፍተኛ አፈጻጸም የታየበት መሆኑ ተገልጿል።
በተለይም በ2018 በጀት ዓመት ሁለተኛ መንፈቅ ዓመት የለውጥ ሥራዎች በመተግበራቸው በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ የውጭ ምንዛሬን ጨምሮ ከፍተኛ ገቢ መገኘቱንና ከትርፍ አኳያም ከታክስ በፊት የተሻለ ትርፍ መመዝገቡን የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ የሺእመቤት ነጋሽ ተናግረዋል።
ለውጤቱ መገኘት በነባራዊ ሁኔታ ላይ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ለተለዩ ተግዳሮቶች የቀረቡ መፍትሔዎች፣ የአሠራር ሥርዓቶች መሻሻል፣ የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች ቅንጅታዊ አሠራር፣ ከፌደራልና ከክልል የባለድርሻ አካላት ጋር የተፈጠረ የሥራ ግንኙነትና የገበያ ዕድል እንዲሁም ወጪ ቆጣቢ አሠራር በዋናነት እንደሚጠቀሱ ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ አብራርተዋል።
ኮርፖሬሽኑ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ዘርፈ ብዙ ጥረት ውስጥ የሚጠበቅበትን ድርሻ ለማበርከት፣ የተቋቋመበትን ተግባርና ኃላፊነት በመከለስ የተዘጋጁ ፍኖተ ካርታና ስትራቴጂያዊ ዕቅድ ከ2019 በጀት ዓመት ጀምሮ እንደሚተገበሩ ወይዘሮ የሺእመቤት አስታውቀዋል።
በመጨረሻም ለ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ መሳካት የኮርፖሬሽኑን የሥራ አመራር ቦርድ፣ የተቋሙን የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስን፣ የግብርና ሚኒስቴርን፣ የኢትዮጵያ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩትን፣ የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽንን እንዲሁም ድጋፍ ያደረጉ ሌሎች የፌዴራልና የክልል የባለድርሻ አካላትን አመስግነዋል።
###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!



