አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፦ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን አነስተኛ የእርሻ መሬት ላላቸው አርሶ አደሮችና ባለሃብቶች የቼክ ሪፐብሊክ ምርት የሆኑ 24 ትራክተሮችን አቀረበ፡፡
‘ዜቶር’ ተብለው የሚታወቁት እነዚህ ትራክተሮች 95 የፈረስ ጉልበት ያላቸው ሲሆን፣ በኮርፖሬሽኑ የኢንጂነሪንግና መገጣጠሚያ የሥራ ክፍል በራስ አቅም ተገጣጥመው ለገበያ ቀርበዋል፡፡
ትራክተሮቹ ሙሉ መለዋወጫና ተቀጽላ መሣሪያዎች ያሏቸው መሆኑን የኮርፖሬሽኑ የእርሻ መሣሪያዎች አቅርቦት ዘርፍ ተወካይ ወ/ሮ ናፈቁሽ ደሴ ገልጸዋል።
ኮርፖሬሽኑ ከ’ዜቶር’ አምራች ኩባንያ ጋር በመተባበር ከሽያጭ በኋላ ለደንበኞች የቴክኒክና ሞያ ሥልጠናና የምክር አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡
በተመሳሳይ ኮርፖሬሽኑ ስንዴ፣ በቆሎ፣ አኩሪ አተርና ሱፍ አጭደው የሚሰበስቡ ‘ዙምላየን’ በመባል የሚታወቁ 190 የፈረስ ጉልበት ያላቸው ቻይና ሠራሽ አጭዶ መውቂያዎችን (Combine harvester) በድጋሚ ለደንበኞቹ ማቅረቡን አስታውቀዋል።
ከዚህ ባሻገር የተለያዩ የፈረስ ጉልበት ያላቸው የጣልያን ስሪት ትራክተሮች፣ ቆሞ መውቂያዎች፣ መከስከሻዎች፣ ማረሻዎች፣ መስመር ማውጫዎች፣ የኬሚካል መርጫ መሣሪያዎች፣ ጎማዎች፣ ፊልትሮዎች፣ የመዳብ ሽቦዎችና የውኃ ፓምፖች በክምችት ይገኛሉ ብለዋል።
###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!




