አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 9 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፦ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከፍተኛ አመራሮች በሞጆ ደረቅ ወደብ በመገኘት የአፈር ማዳበሪያ ሥርጭት ሂደትን ተመልክተዋል።
በኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ የሺእመቤት ነጋሽ የተመራው የተቋሙ የበላይ አመራር ከጂቡቲ ወደብ በባቡር ተጓጉዞ ሞጆ ደረቅ ወደብ የደረሰ ማዳበሪያና ከወደቡ በኢትዮጵያ ባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ተሽከርካሪዎች አማካኝነት ወደ አርሶ አደሮች የኅብረት ሥራ ማኅበራት የሚደረገውን ሥርጭት ቃኝቷል።
በዚሁ ወቅት የሞጆ ደረቅ ወደብ የሥራ ኃላፊዎች ስለ ኦፕሬሽኑ አጠቃላይ ሂደት ገለጻ አድርገዋል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ የሺእመቤት ነጋሽ፣ የአፈር ማዳበሪያን ለአርሶ አደሩ በወቅቱ ለማድረስ የባቡር ፉርጎዎችንና የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎችን በማቀናጀት ሥርጭቱን ይበልጥ ለማቀላጠፍ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የግብርና ሚኒስቴር በየዓመቱ እያጠና በሚያቀርበው የሀገሪቱ የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት መሰረት የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከተቋቋመበት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ የማዳበሪያ ግዥ በመፈጸም ላይ ይገኛል።
###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!





