አዲስ አበባ፣ መጋቢት 22 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢግሥኮ):- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ በዋና መ/ቤትና በአዳማ ቅርንጫፍ ለሚያገለግሉ 126 የቀን ሠራተኞች ማእድ አጋራ።
በኮርፖሬሽኑ ዋና መ/ቤት መጋቢት 22 ቀን 2018 ዓ.ም ለተካሄደው ማእድ ማጋራት ከ600 ሺህ ብር በላይ ወጪ የምግብ ዘይትና አልባሳት የተገዛ ሲሆን፣ አይሚ ገዳ የምግብ ኮምፕሌክስ የተባለ ድርጅት በስፖንሰርነት 20 ኩንታል የስንዴ ዱቄት ድጋፍ አድርጓል።
ኮርፖሬሽኑ ወደ ውጭ ገበያ በሚልከው የእጣንና የሙጫ ምርት ዝግጅት ላይ ለተሰማሩ 37 የአዳማ ቅርንጫፍ ሴት የቀን ሠራተኞች ከማእድ ማጋራት በተጨማሪ አልባሳት ተበርክቶላቸዋል።
በዕለቱ የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ የሺእመቤት ነጋሽ ባስተላለፉት መልእክት፣ በሀገረ መንግሥት ግንባታና በሰላም ማስፈን ረገድ የሴቶች ተሳትፎና ጥበብ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው፣ በቀጣይም ሴቶች ከወንድ አጋሮቻቸው ጋር በመሆን የሀገሪቷን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የበኩላቸውን አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ አሳስበዋል።
በተለይም ግብርናን በማዘመን የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ርብርብ ውስጥ የኮርፖሬሽኑ ሴቶች ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የአዳማ ቅርንጫፍ ሴት የቀን ሠራተኞች በሰጡት አስተያየት “ተረስተን ነበር፤ አሁን ግን አስታዋሽ በማግኘታችን እናመሰግናለን” ብለዋል።
በኮርፖሬሽኑ የሥርዓተ ጾታ እኩልነትን እና የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ሪፖርት በሞያ ደኅንነትና ጤንነት አገልግሎት ቡድን መሪ ወ/ሮ ወይንሸት ገለሶ የቀረበ ሲሆን፣ በሥርዓተ ጾታና ሴቶችን በማብቃት ዙሪያ በሒሩት በቀለ (ዶ/ር) ገለጻ ተደርጓል።
###
50 ዓመት የሴቶች ድምፅ ለእኩልነትና ለበለፀገች ኢትዮጵያ!







