ባሕር ዳር፡ መጋቢት 11/2018 ዓ.ም (አሚኮ):- የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ግብርናውን በማዘመን ምርታማነትን ለማረጋገጥ በግብዓት አቅርቦት፣ ሜካናይዜሽን ማስፋት እና በውጤታማነት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አሥፈጻሚ የሺእመቤት ነጋሽ የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዘርፉን ለማዘመን የአፈር ማዳበሪያ እና ምርጥ ዘር አቅርቦትን ከማሳለጥ ባለፈ የግብርና ሜካናይዜሽንን በስፋት ተደራሽ የማድረግ ሥራ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን ተናግረዋል።
በዓመቱ እስከ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ (ዳፕ እና ዩሪያ) ለማቅረብ አቅዶ እየሠራ መኾኑም ገልጸዋል።
እስካሁንም 1ነጥብ 5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ግዥ ተፈጽሞ የማከፋፈል ሥራው ቀጥሏል ብለዋል። ለአማራ ክልል የሚያስፈልገውን 8 ነጥብ 2 ሚሊዮን ኩንታል ግብዓት ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መኾኑን ገልጸዋል።
እስካሁንም 2 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታሉ ወደ ክልሉ ገብቶ በመሰራጨት ላይ መኾኑን ተናግረዋል። ከማዳበሪያ ባሻገር በየዓመቱ 460 ሺህ ኩንታል ሥነ-ምህዳሩን ያገናዘበ ምርጥ ዘር እየቀረበ መኾኑን ዋና ሥራ አሥፈጻሚዋ ገልጸዋል።
ለአማራ ክልልም እንደ አኩሪ አተር፣ ሩዝ፣ በቆሎ እና ጤፍ ያሉ ምርጥ ዘሮች በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደሮች እንዲደርሱ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ግብርናውን ከሞፈር እና ቀንበር ለማላቀቅ የሚደረገው የሜካናይዜሽን ሽግግር የዘርፉ ማዕከል መኾኑንም አንስተዋል።
ይህን ሂደት ዘላቂ ለማድረግም ኮርፖሬሽኑ በሦሥት ዋና ዋና ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሠራ ይገኛል። የመጀመሪያው የቆሙ የጥገና ማዕከላትን በማደራጀት እና የመለዋወጫ እቃዎችን በማቅረብ አገልግሎቱን ማስቀጠል ነው።
ሁለተኛው ደግሞ በሀገር ውስጥ የመገጣጠም ሥራ እስከሚጀመር ድረስ ጥራታቸውን የጠበቁ፣ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት ሊሰጡ የሚችሉ የተለያዩ የፈረስ ጉልበት ያላቸውን ትራክተሮች፣ ኮምባይነሮች፣ የውኃ መሳቢያ ሞተሮች እና ሌሎችም የእርሻ መሳሪያዎችን የደንበኛውን ፍላጎት ታሳቢ ባደረገ መንገድ ከውጭ በማስገባት ተደራሽ ማድረግ ነው ብለዋል። በዘላቂነት ደግሞ በሀገር ውስጥ ለመገጣጠም መታቀዱን ነው ያስታወቁት።
ሦሥተኛው እና ለአነስተኛ አርሶ አደሮች ትልቅ እፎይታ የሚሰጠው ደግሞ የሜካናይዜሽን መሣሪያዎችን በኪራይ በማቅረብ ከመሬት ዝግጅት እስከ ምርት ሥብሠባ ያለውን ሂደት ማዘመን ነው። እነዚህ የተቀናጁ ጥረቶች የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ ኢትዮጵያን በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ በዓለም አቀፍ ደረጃ ግንባር ቀደም የስንዴ እና የበቆሎ አምራች ሀገር ለማድረግ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት መሠረት የሚጥሉ ናቸው ተብሏል።

