ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ የሺመቤት ነጋሽ ከተመራ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ሉዕክ ጋር በግብርና ግብዓት፤ ምርጥ ዘር፤ በዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎች አቅርቦትና ዘርፉን ለማዘመን በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ የክልሉ መንግስት ግብርናን ለማዘመንና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ በገበያ ተፈላጊ የሆኑና የኤክስፖርት ምርቶች ምርታማነትን በማሳደግ ከግብርናው ዘርፍ የሚገኝ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማላቅ በትኩረት በመስራት ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ክልሉ በርካታ ፀጋዎች ያሉት መሆኑን የገለጹት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ባለፉ ጊዜያት በክልሉ በግብርናው ዘርፍ ያሉ እምቅ የመልማት አቅሞችን በጥናት በመለየት እንዲሁም ለማዳበሪያና ዘር አቅርቦት እና የአርሶ አደሩን የግብዓትና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ለማሻሻል ተገቢውን ትኩረት በመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ክልሉ የግብርና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በክልሉ ከሚገኙ የግብርና የምርምር ጣቢዎች በተጨማሪ የምርጥ ዘር ድርጅት በማቋቋም ጭምር ውጤታማ ስራዎች በመሰራት ላይ እንደሚገኝም ጨምረው አብራርተዋል።
ምርታማነትን ለማሳደግ የዘር አቅርቦት ወሳኝ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ውይይቱ የምርጥ ዘር አቅርቦትን እና ፍላጎትን ከማጣጣም አኳያ ያሉ ችግሮችን ከኮፕሬሽኑ ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።
ርዕሰ መሰተዳድሩ የግብርና ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን በማልማት ምርታማነትን ከማሳደግ ባሻገር፤ የቴክኖሎጂ ሽግግርን በማሳለጥ የክልሉን ግብርና በማዘመኑ ረገድ ጉልህ ሚና በመጫወት ላይ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን እንደ ሀገር የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን በመደረግ ላይ ያሉ ጥረቶችን በማገዝ ጉልህ አስትዋጽ በማበርከት ላይ ይገኛል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ኮርፖሬሽኑ በክልሉ በተቀናጀ የግብርና ግብዓት አቅርቦት እና ሜካናይዜሽን ለመስራት ማቀዱ የክልሉን ግብርና ለማዘመን ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ሁለንተናዊ ልምድ እና አቅም ያለው መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግስት ኮርፖሬሽኑ ላቀዳቸው ስራዎች ውጤታማነት አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ በቅንጅት የሚሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ክልሉ የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን ዘመናዊ የእርሻ ማሽነሪዎችን እና መካናይዜሽንን ለማስፋፋት በማድረግ ላይ ያለውን ጥረት ኮርፖሬሽኑ በሙሉ አቅሙ ድጋፍ በማድረግ እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።
የኮርፖረሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ የሺመቤት ነጋሽ በበኩላቸው፤ ውይይቱ ከክልሎች ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ምርታማነት በማሳደግ የሀገርን የምግብ ሉዓላዊነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ ስራዎች ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮርፖሬሽኑ በክልሉ የግብርና ግብዓት አቅርቦት ለማሳደግ እንዲሁም ዘርፉን ለማዘመን በሚደረገው ጥረት ከክልሉ መንግስት ጋር በመቀናጀት የሚሰራ መሆኑን ገልፀዋል።







