አዲስ አበባ፣ የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፦ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን እና የግሪን አግሮ ሶሉሽን የግል ኩባንያ (‘ለእርሻ’) አመራሮች በግብርናው ዘርፍ በጋራ መሥራትና ለውጥ ማምጣት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የካቲት 2 ቀን 2018 ዓ.ም ተወያዩ።
በኮርፖሬሽኑ ዋና መ/ቤት በተካሄደው በዚህ ውይይት ላይ የሁለቱ ተቋማት አመራሮች አነስተኛ ማሳ ያላቸውን አርሶ አደሮች በጋራ ለመደገፍ በሚያስችሉ አማራጮች ላይ መክረዋል።
ውይይቱ በዋነኛነት ዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም የአነስተኛ አርሶ አደሮችን የፋይናንስ አቅም ማሻሻል፣ የግብርና ግብዓቶችና የመካናይዜሸን አገልግሎት ተጠቃሚነትን ማሳደግ እንዲሁም የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በሥልጠና ማጎልበት ላይ ያተኮረ ነበር።
በውይይቱ ማጠቃለያ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ የሺእመቤት ነጋሽ የትብብር ዘርፎችን በዝርዝር የሚያጠናና የስምምነት ሰነድ (MoU) የሚያዘጋጅ የጋራ ኮሚቴ እንዲቋቋም በሰጡት አቅጣጫ መሰረት በኮርፖሬሽኑ በኩል የኮሚቴ አባላት የተሰየሙ ሲሆን፣ በኩባንያው በኩልም እንደሚቋቋም ተገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሁለቱ ተቋማት ኮሚቴዎች በትብብር ለመሥራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከመከሩ በኋላ ተቋማቱ የመግባቢያ ስምምነት (MoU) በቅርቡ እንደሚፈራረሙ ይጠበቃል።
‘ለእርሻ’ – በግሪን አግሮ ሶሉሽን የግል ኩባንያ የተቋቋመ የዲጂታል መድረክ (Platform) ሲሆን፣ ዘመናዊ የመገናኛ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም አነስተኛ አርሶ አደሮችን ከግብርና ግብዓት (ዘር፣ ማዳበሪያ፣ አግሮኬሚካል) አቅራቢዎች፣ ከመካናይዜሽን አገልግሎት ሰጪዎች፣ ከፋይናንስ ተቋማትና ከገበያ ጋር እንደሚያስተሳስር በውይይቱ ተብራርቷል። ከአየር ንብረት ጋር በተያያዘም የምክር አገልግሎት እንደሚሰጥ ታውቋል።
በአጠቃላይ ‘ለእርሻ’ – ለምርታማነት እድገትና ለቴክኖሎጂ ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚያበረክት በውይይቱ ወቅት ተገልጿል።
###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!


