ወላይታ ሶዶ፣ ጥር 28 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፦ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከክልል የግብርና ቢሮዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ስትራቴጂያዊ አጋርነት በመፍጠርና በቅርበት በመሥራት ለግብርና ምርታማነትና ለምግብ ሉዓላዊነት መረጋገጥ እንደሚሠራ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገለጹ።
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ወ/ሮ የሺእመቤት ነጋሽ ይህንን የገለጹት፣ በግብርና ግብዓት አቅርቦት ዙሪያ ጥር 28 ቀን 2018 ዓ.ም በወላይታ ሶዶ ከተማ በኃይሌ ሆቴል በተካሄደ የምክክር መድረክ ላይ ነው።
በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፣ ኮርፖሬሽኑ በአርሶ አደሮች ተፈላጊ የሆኑ ዘሮችን እንዲሁም ከአዋጭነት አኳያ በመንግሥትና በግል ዘር አባዥዎች የማይባዙ ዘሮችን አባዝቶ በማቅረብ የልማትና የገበያ ክፍተትን ለመሙላት እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አማካሪ የሆኑት አቶ አበራ ለማ በበኩላቸው፣ ኮርፖሬሽኑና የክልል ግብርና ቢሮዎች አንድ የግብርና ቤተሰብ በመሆናቸው ተቀናጅተውና ተናበው በጋራ እንዲሠሩ ጠይቀዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ኮርፖሬሽኑ የግብርና ሞተር መሆኑን ጠቁመው፣ ክልሉ ሰፊ የግብርና አቅም እንዳለው በመግለጽ ኮርፖሬሽኑ በክልሉ ቅርንጫፍ አቋቁሞ በይበልጥ በቅርበት በጋራ እንዲሠራ ጠይቀዋል።
ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መኮንን ጋሶ እንደተናገሩት፣ ኮርፖሬሽኑ ለክልሉ አርሶ አደሮች የግብርና ግብዓቶችን ለዓመታት በማቅረብ ባለውለታ ተቋም ነው። ለዚህም ምስጋናና ክብር እንዳላቸው ገልጸው፣ በቀጣይም አብሮ ለመሥራት ዝግጁነታቸውን አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ የሀዲያ ዞን የግብርና ግብዓት ቡድን መሪ አቶ ሳልማን ኤርገኖ በሰጡት አስተያየት፣ ኮርፖሬሽኑ በዘር ጥራት ምሳሌ እንደሆነና ከዚህም የተነሳ በአካባቢው አርሶ አደሮች ተመራጭ መሆኑን ተናግረዋል።
በሌላ በኩል ኮርፖሬሽኑ የመስክ የሰርቶ ማሳያ በማዘጋጀት የዘር ማስተዋወቅ ሥራን አጠናክሮ እንዲቀጥል፣ አዳዲስ የዘር ዝርያዎችን በማባዛት እንዲያቀርብ፣ አግሮኬሚካሎችን በስፋት በማቅረብ ገበያውን እንዲያረጋጋ እንዲሁም የግብዓት ማዕከላትን በተለያዩ አካባቢዎች በመገንባት አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽ እንዲያደርግ የውይይቱ ተሳታፊዎች አስተያየት ሰጥተዋል።
በዕለቱ የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ፍሬሕይወት ጠምስ እና በኮርፖሬሽኑ የምርጥ ዘር አቅርቦት ዘርፍ የዘር ምርት ዝግጅትና ሥርጭት መምሪያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ማሩ ደገፋ ለውይይት መነሻ የሚሆን ገለጻ አቅርበዋል።
በውይይቱ ላይ ከሲዳማ፣ ከማዕከላዊ ኢትዮጵያና ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች የግብርና ቢሮዎች እንዲሁም ከኦሮሚያ ክልል የምዕራብ አርሲ ዞን የግብርና መምሪያዎች የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዘር ጥራት ተቆጣጣሪዎችና የአርሶ አደሮች የኅብረት ሥራ ማኅበራት ሥራ አስኪያጆች ተገኝተዋል።
###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!