አዲስ አበባ፣ ጥር 2/2018 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፡-የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ከ8.2 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በአማራ ክልል በባህር ዳር ከተማ ት/ቤትና የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤት ሊያስገነባ ነው።
ሁለቱም ግንባታዎች በማኅበራዊ ኃላፊነት በጀት የሚፈጸሙ ሲሆን፣ የማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተከናውኗል።
በዚህ መሰረት የዶና በርበር የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሉዓለም አቤ (ዶ/ር) እና የት/ቤቱ ርዕሰ መምህር እንዲሁም የኮርፖሬሽኑ የባህር ዳር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ እርቄ ገላውና የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ታህሳስ 24 ቀን 2018 ዓ.ም የአራት የመማሪያ ክፍሎች የግንባታ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ተከናውኗል።
በተመሳሳይ ሁለት ህመምተኛ ልጆች ያሏቸውን የእማሆይ እናንዬ ታመነ መኖሪያ ቤት ግንባታን ለማስጀመር ጥር 2 ቀን 2018 ዓ.ም መርሐ ግብር ተካሄዷል።
በመርሐ ግብሩ ላይ የጣና ክፍለ ከተማ አስተዳደር አመራሮች እና የኮርፖሬሽኑ የባህርዳር ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ እርቄ ገላውና የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
ኮርፖሬሽኑ ባለፉት ሁለት ዓመታት ካከናወናቸው ትላልቅ የማኅበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች ውስጥ በ2016 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ባሌ ሮቤ ከተማና በአዲስ አበባ ከተማ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ያስገነባቸው የአቅመ ደካማ መኖሪያ ቤቶች (የውስጥ ቁሳቁስ በማሟላት) እንዲሁም በ2017 ዓ.ም በትግራይ ክልል ማዕከላዊ ዞን ያስገነባው የውቅሮ ማራይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አራት የመማሪያ ክፍሎች (ወንበር፣ ጠረጴዛና ሰሌዳ በማሟላት) ይጠቀሳሉ።
###
ግብርናን ከማዘመን ጎን ለጎን ማኅበራዊ ኃላፊነታችንን እንወጣለን!




