ቢሾፍቱ፣ ታህሳስ 25/2018 ዓ.ም (ኢግሥኮ):- የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በሦስት የዳሰሳ ጥናት ቡድኖች ሲያካሂድ የቆየው የተቋሙ የነባራዊ ሁኔታ የዳሰሳ ጥናት ለኮርፖሬሽኑ ሥራ አመራር ለውይይት ቀረበ።
ውይይቱ ከዛሬ ታህሳስ 25 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት ቢሾፍቱ በሚገኘው ያዴን ሆቴል ይቀጥላል።
በጥቅምት ወር መጨረሻ የተጀመረው የዳሰሳ ጥናት ዋና ዓላማ፣ የኮርፖሬሽኑን አጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታ በመገምገም ተቋሙ በቀጣይ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ፣ ምርታማና አትራፊ ሆኖ እንዲቀጥል ለማስቻል መሆኑን የጥናት ሪፖርቱን ያቀረቡት የኮርፖሬሽኑ የእርሻ መሣሪያዎችና የግብርና ውጤቶች አቅርቦት ዐቢይ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተከስተ ክፍሌ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
የዳሰሳ ጥናቱ ድርጅታዊ መዋቅር እንዲሁም የሰው ኃይል አስተዳደር፤ የአሠራር ሥርዓትና ሂደቶች፤ የአቅርቦትና ንብረት አስተዳደር፤ የማዳበሪያ፣ የአግሮኬሚካሎች፣ የምርጥ ዘር፣ የግብርና ውጤቶች፣ የተፈጥሮ ሙጫ ምርቶችና የእርሻ መሣሪያዎች አቅርቦት፤ የሜካናይዜሽን፣ የትራንስፖርትና የጥገና አገልግሎቶች፤ ገበያና ሽያጭ፤ የፋይናንስ አሠራርና የመረጃ አስተዳደር ሥርዓት መስኮችን ያካተተ መሆኑን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል።
በጥናቱ ችግሮች፣ ጥንካሬዎች፣ መልካም አጋጣሚዎችና ስጋቶች መለየታቸውን ያስታወቁት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ የተቋሙን መዋቅራዊ አደረጃጀት በመፈተሽ፤ የዋና መ/ቤት፣ የዘርፎችና የቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች የሥራ መሪዎችና ከፍተኛ ባለሞያዎችን በመጠየቅ እንዲሁም ውስጣዊና ውጫዊ መረጃዎችን በመተንተን ጥናቱ መከናወኑን አብራርተዋል።
በመጨረሻም በጥናት ግኝት የተለዩ ቁልፍ ችግሮችን፣ የችግሮቹ መነሻ መንስኤዎችን፣ ያሳደሩት ተጽዕኖዎችን፣ የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎችን እንዲሁም ጠንካራ ጎኖችን፣ ክፍተቶችን፣ መልካም እድሎችን እና ስጋቶችን መሰረት በማድረግ ምክረ ሀሳቦች መቅረባቸውን አስታውቀዋል።
በውይይቱ ላይ የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ የሺእመቤት ነጋሽን ጨምሮ የተቋሙ ሥራ አመራር እና የጥናት ቡድን አባላት ተገኝተዋል።
###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!



