ቱም፣ ታህሳስ 12 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፦ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በምዕራብ ኦሞ ዞን እያለማ የሚገኘው የኮካ እርሻ ልማት ተጎበኘ።
ታህሳስ 12 ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደው ጉብኝት ላይ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የግብርና እና የሠላምና ፀጥታ ቢሮዎች አመራሮች፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ ተወካይ፣ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የምዕራብ ኦሞ ዞን፣ የማጂና ሱሪ ወረዳዎች አስተዳዳሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የኮርፖሬሽኑ የግብርና ውጤቶች ሽያጭና የሜካናይዜሽን አገልግሎት ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዘነበ ወልደሥላሴ ባደረጉት ገለጻ፣ ኮርፖሬሽኑ በኮካ እርሻ ልማት በ143 ሄክታር መሬት ላይ የሩዝ፣ በቆሎ፣ ሰሊጥና አኩሪ አተር ሰብሎችን በሙከራ ደረጃ ማምረቱንና ተስፋ ሰጪ ውጤት መገኘቱን አስታውቀዋል።
የእርሻ መሣሪያዎች አቅርቦት ዘርፍ ሥራ አስፈጻሚ አቶ አስማማው ግዛቸው በበኩላቸው፣ 5 ሺህ ሄክታር ስፋት ያለውን የኮካ እርሻን ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ለማስገባት የመሬት ዝግጅት ሥራዎች በስፋት እየተከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የጉብኝቱ ተሳታፊዎችም ኮርፖሬሽኑ በክልሉ እያካሄደ የሚገኘው የግብርና ኢንቨስትመንት አበረታችና የሚደነቅ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮርፖሬሽኑ ምርጥ ዘር እና ወደ ውጭ የሚላኩ የቅባት እህሎችን ለማምረት የኮካ እርሻን ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ተረክቦ በሙከራ ደረጃ ወደ ሥራ የገባው በ2017 ዓ.ም አጋማሽ ላይ ነበር።
የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በክልሉ ሦስተኛ የልማት መዳረሻው ከሆነው የኮካ እርሻ ልማት በተጨማሪ የታማሻሎ የምርጥ ዘር ማባዣ እርሻ ልማት እና የቦንጋ የተቀናጀ የግብርና ግብዓትና የሜካናይዜሽን አገልግሎት ማዕከልን በክልሉ ውስጥ አቋቁሞ እያስተዳደረ ይገኛል።
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!



