“ኮርፖሬሽኑ ፍትሐዊ የልማት ዕድል ይዞ ስለመጣ እናመሰግናለን።” የምዕራብ ኦሞ ዞን የመንግሥት ተጠሪ
ቱም፣ ታህሳስ 13 ቀን 2018 ዓ.ም (ኢግሥኮ)፦ የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በኮካ እርሻ ልማት ቀጣይ ሥራዎች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ታህሳስ 12 ቀን 2018 ዓ.ም ውይይት አድርጓል።
በማጂ ወረዳ ቱም ከተማ አስተዳደር የመሰብሰቢያ አዳራሽ የተካሄደውን የውይይት መድረክ የመሩት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሠላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ዓለሙ፣ የኮርፖሬሽኑ የእርሻ መሣሪያዎችና የግብርና ውጤቶች አቅርቦት ዐቢይ ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተከስተ ክፍሌ (ዶ/ር) እና የምዕራብ ኦሞ ዞን የመንግሥት ተጠሪ አቶ በድሉ መዓዛ ናቸው።
በውይይቱ ማጠቃለያ የኮካ እርሻ ልማት የጋራ ልማት መሆኑን የጠቆሙት የክልሉ የሠላምና ፀጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ዓለሙ፣ ከፌደራልና ክልል የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአካባቢውን ፀጥታ በዘላቂነት ለመጠበቅ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
የምዕራብ ኦሞ ዞን የመንግሥት ተጠሪ አቶ በድሉ መዓዛ በበኩላቸው፣ የምዕራብ ኦሞ አካባቢ በግብርና እና በማዕድን ሀብት የበለፀገ ቢሆንም ጠረፍ አካባቢ ስለሚገኝ በቀደሙት ማዕከላዊ መንግሥታት የተረሳና በልማት ወደ ኋላ የቀረ እንደነበረ አስታውሰው፣ ኮርፖሬሽኑ ይህንን ክፍተት የሚሞላ ፍትሐዊ የልማት ዕድል ይዞ በመምጣቱ አመስግነዋል።
የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተከስተ ክፍሌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የኮካ እርሻ ልማት ለአካባቢው አርብቶ አደሮች እርሻን የሚያላምድ፣ በግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግርና በግብዓት አቅርቦት ዙሪያ እንዲሁም በሥራ እድል ፈጠራ መሠረታዊ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን አስረድተዋል።
የማጂና ሱሪ ወረዳዎች አስተዳዳሪዎች እንዲሁም የአካባቢው ነዋሪዎች የኮካ እርሻ የሥራ ዕድል በመፍጠር የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ገልጸው፣ ለእርሻው ውጤታማነት ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
###
ግብርናን ማዘመን ግባችን ነው!









